አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለኮሮናቫይረስ ለመከላከልና ሕክምና የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አበረከተ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ሕክምና  የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሐምሌ 9/2012 ዓ/ም ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በሆስፒታሉ ተገኝተው የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በቀጣይ ዩኒቨርሲቲውና ሆስፒታሉ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

የጋሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ማሄ ቦዳ ዩኒቨርሲቲው የሆስፒታሉን ችግሮች ተረድቶ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጉልህ ሚና ያበረከታል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሁለቱ ተቋማት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው አሁን ላይ በሆስፒታሉ ያለው የሥራ እንቅስቃሴና አደረጃጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን ሆስፒታሉን ተዘዋውረው ባዩ ጊዜ መታዘባቸውን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው መሰልና ሙያዊ ድጋፎች ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የአስተዳደር ጉ/ም/ ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በበኩላቸው በሁለቱ ተቋማት መካከል የተጀመረው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመው በዋናነት የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ የሆስፒታሉን ባለሙያዎች ለማብቃት  በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት በቀጣይነት ድጋፍ እንደሚያደረግም ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ጨንቻ ሆስፒታልን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱ መሆኑን ገልጸው ሆስፒታሉ ያለው መዋቅርና አደረጃጀት ከገመቱት በላይ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ሆስፒታሉ ተማሪዎችን ለተግባር ትምህርት በመላክ እንዲሁም የተለያዩ በኮሌጁ የሚገኙ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ተመላልሰው በሆስፒታሉ አገልግሎት እንዲሰጡና ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የጨንቻ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድማገኝ ንጋቱ የጨንቻ ሆስፒታል በ1953 ዓ/ም የተመሠረተ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ የሆስፒታሉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥና ደረጃ ለማሳደግ በምናደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ጉልህ ሚና ያበረክታል ብለው እንደሚያምኑና በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅትና በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ሳኒታይዘር፣ የሙቀት መለኪያ፣ አንሶላ፣ ብርድ-ልብስና ፍራሽ ዩኒቨርሲቲው ለሆስፒታሉ ያደረጋቸው ድጋፎች ናቸው፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት