የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዞችን ሐምሌ 20/2012 ዓ/ም ጉብኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ጉብኝቱ በዩኒቨርሲቲው ያሉ የተለያዩ የገቢ ማመንጫ ተቋማት ያሉበትን የአፈፃፀም ደረጃና ችግሮች በአካል በማየት ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫና ውሳኔ ለመስጠት የሚረዱ ሀሳቦች ለማግኘት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ወጪያቸውን በከፊል እንዲሸፍኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በ2007 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የሕትመትና የግብርና ኢንተርፕራይዞች ተመስርተው ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ም/ፕሬዝደንቷ መሰል ጉብኝቶች መደረጋቸው የዘርፉን ወጤታማነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከዚህ ቀደም የነበረው የኢንተርፕራይዞቹ አደረጃጀት ለአሠራር ምቹና ለውጤታማነት አንዱ ተግዳሮት መሆኑ ከግንዛቤ ወስጥ በመግባቱ ከዚህ ቀደም የነበሩት 3 ኢንተርፕራይዞችን ወደ አንድ በማምጣት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ባወጣው የኢንተርፕራይዝ ማቋቋሚያ መመሪያ ቀጥር 1/2012 ዓ/ም መሠረት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገቢ ማመንጫ ድርጅት የካቲት 2012 ዓ/ም መቋቋሙን ወ/ሮ ታሪኳ ገልፀዋል፡፡ አሁን ላይ የገቢ ማመንጫ ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ም/ፕሬዝደንቷ የድርጅቱ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የገቢ ማመንጫ ድርጅቶቹ ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ችግሮችን ያሳለፉ ሲሆን የድርጅቶቹ አደረጃጀት፣ መዋቅርና አሠራረር ለማሻሻል ባለፈው በጀት ዓመት በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በተደረገው የመስክ ጉብኝትም በተቋማቱ ያሉ አቅሞችንና ተግዳሮቶችን ማወቅና መለየት መቻሉን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ከጉብኙቱም በኋላ ከአመራሩ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ የማሻሻያ ሀሳቦች ተሰብስበው ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በመስክ ጉብኝቱ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ገቢ ለማመንጨት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለው መገንዘባቸውን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም እነዚህን አቅሞችና መልካም አጋጣሚዎች በአግባቡ ለመጠቀም በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የጉብኝት ፕሮግራሙ የችግኝ ተከላ በማካሄድ ተጠናቋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት