አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እያስገነባ የሚገኘውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታን በ2013 በጀት ዓመት በከፊል ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የሆስፒታሉን የግንባታ ሂደት ነሐሴ 15/2012 ዓ/ም በጎበኙበት ወቅት ተገልጿል፡፡

በ2007 ዓ/ም የተጀመረው የሆስፒታሉ ግንባታ በዲዛይን ማስተካከያና ተጨማሪ ግንባታ፣ በሆስፒታሉ ግንባታ ቦታ ተነሺዎች፣ የክፍያዎች መዘገየት፣ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት፣ በግንባታ አካባቢ የሚገኙ የመብራት፣ የውሃና የስልክ መስመሮች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ የዘገየ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት 77 በመቶ የግንባታ ሂደት መጠናቀቁ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን የሆስፒታሉ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ካደረጉ ምክንያቶች ከዲዛይን ጋር ተያይዘው የነበሩ ችግሮች መሠረታዊና ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የግንባታ ሂደት ሆስፒታሉን በ2013 በጀት ዓመት በከፊል ወደ ሥራ ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መድረሱን የተናገሩት ወ/ሮ ታሪኳ በግንባታ ሂደት ወስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የኤሌክትሮ-ሜካኒካል ዕቃዎች ግዥ ከአሳንሳር በስተቀር ወደ ሀገር ወስጥ በመግባታቸው የመገጣጠም ሥራውም እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታሉን በ2013 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እንደሚሠራ ገልፀው የግንባታ ሂደቱን ለመጠናቅቅ ይረዳ ዘንድ ከተነሺ ግለሰቦችና መነሳት ያለባቸው የውኃ፣ የስልክና የመብራት መስመሮችን ለማንሳት ክፍያ ስለተፈፀመ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡ የግንባታ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሆስፒታሉን በተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ማሟላት ትልቅ ተግባር መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳምጠው ለዚህም ዩኒቨርሲቲው የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የሆስፒታሉን መጠናቀቅ የአካባቢው ማኅበረሰብም ጭምር በጉጉት የሚጠብቀው በመሆኑ የግንባታ ሂደቱ ያለበት ሁኔታ የሚበረታታ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ወስጥ አጠናቆ ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ይርጋለም ኮንስትራክሽን በተሰኘ የግንባታ ተቋራጭ ከ970 ሚሊየን ብር በላይ በጀት እየተገነባ የሚገኘው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል 575 የታካሚ አልጋዎች ያሉት ግዙፍ ሆስፒታል ሲሆን የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ ከመማር ማስተማርና የምርምር ሥራዎች ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ የሕክምና ትምህርት ቤትን በመያዝ 7ኛው የዩኒቨርሲቲው ካምፓስ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነም ማወቅ ተችሏል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት