በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል በማቴሪያል ፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም ለመክፈት የውጭ ሥርዓተ ትምህርት ነሐሴ 18/2012 ዓ/ም ግምገማ አካሂዷል፡፡

የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትውልድና የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በማስፋፋትና በጥራት መስጠት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በፊዚክስ ትምህርት መስክ የሚከፈተው የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራምም የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል፡፡ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲከፈቱ የሥርዓተ-ትምህርቱ ዝግጅት በርካታ ሂደቶችን እንደሚያልፍ የገለፁት ዶ/ር የቻለ ፕሮግራሞችን መክፈት በራሱ ግብ ባለመሆኑ ሥርዓተ-ትምህርቱን በየጊዜው የመከለስ እንዲሁም ትምህርቱን በጥራት መስጠትና ምርምር ተኮር የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ በቀጣይነት ይሠራል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በ2013 በጀት ዓመት ተጨማሪ ፕሮግራሞችን በመክፈት የፒ ኤች ዲ ፕሮግራሞችን 25 እናደርሳለን ያሉት ዶ/ር የቻለ በዚህም ከፍተኛ ባለሙያዎችንና ተማራማሪዎችን ለሀገሪቱ ማፍራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ በበኩላቸው ኮሌጃቸው በ6 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን ጠቅሰው በ6ቱም የትምህርት መስኮች በማስተማር ሂደት ውስጥ ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች በመጠቀም አዲስ የምንከፍተውን ፕሮግራም በተሻለ ጥራት መስጠት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በኮሌጃችን 7ኛውን የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመክፈት በሥርዓተ-ትምህርቱ ዝግጅት ለተሳተፉ የኮሚቴ አባላት፣ ለፊዚክስ ትምህርት ከፍል መምህራንና ኃላፊው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ ወንድማገኝ አንጁሎ ትምህርት ክፍሉ ፕሮግራሙን ለመጀመር የሚያስችል በቂ የሰው ኃይልና አስፈላጊ ግብዓት ያሟላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ የሚመረቁ ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማኑፋከቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣ በቴሌኮሚዩኒኬሽንና በኃይል ማመንጫ ተቋማት ተፈላጊ እንደመሆናቸው እንደ ሀገር በዘርፉ የተመረቀ የከፍተኛ ባለሙያ ዕጥረት መኖሩ በተደረገው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ረ/ፕ ወንድማገኝ ተናግረዋል፡፡ ሥርዓተ-ትምህርቱ አስፈላጊ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ሥራ እንደሚጀመር ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በሥርዓተ-ትምህርቱ ግምገማ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ሁለት የዘርፉ ምሁራን በሥርዓተ-ትምህርቱ ላይ ያለቸውን ግምገማና አስተያየት በስፋት ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ የተሰጡ አስተያየቶችና የማስተካከያ ሀሳቦች ተካተውበት ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን በ21 የ3ኛ፣ በ99 የ2ኛ እና በ78 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች በማስተማርና በማሰልጠን ለሀገሪቱ እያበረከተ ዘርፍ ብዙ አገራዊ ዕድገት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት