የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኅብረት 39ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከነሐሴ 21-23/2012 ዓ/ም ድረስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ3 ቀናት ተካሂዷል፡፡

መርሃ-ግብሩን በአገር ባህልና ወግ መሠረት መርቀው የከፈቱት የጋሞ አባቶች ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲዎች ሀገርንና ዓለምን የሚለውጡ አዳዲስ ሐሳቦችና ፈጠራዎች የሚፈልቁበት ቦታ እንጂ ተማሪዎች በቋንቋ፣ በብሄርና በሐይማኖት እየተከፋፈሉ የሚጣሉበት ሥፍራ እንዳይሆንና በተቋማቱ ከዚህ ቀደም እየታዩ የነበሩ የሠላም መደፍረሶች እንዳይከሰቱ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የተማሪዎች ኅብረትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ሁሉ አካላት ለሠላም ዘብ በመቆም የአገራችን ብልፅግና እንዲረጋገጥ በትኩረት እንዲሠሩ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከትምህርት ሚኒስቴር ለተገኙ ተወካዮች በባህሉ መሠረት ጥብቅ አደራ ከእርጥብ ሣር ጋር በመስጠት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የብሄር ማንነታችን የሚያብበው እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ስትኖር ነው ያሉት አባቶቹ ሁላችንም ኢትዮጵያ በምትባል ምድር ላይ የተዘራን የሰብል ዓይነቶች በመሆናችን የሀገራችንን ህልውና ልናስጠብቅ እንደሚገባ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችና መምህራን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኢዶሳ ተርፋሳ ጊዜው ተስፋችንን የሚፈታተን ቢሆንም ከችግሩ አሻግረን ተስፋችንን እያየን ስለወደፊቱ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁኔታ ላይ በመወያየት እንዲሁም የአመራር ክሂሎትና ዕውቅት ከማዳበር አንፃር ጉባዔው ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡ የተማሪዎች ኅብረት አመራሮች በዩኒቨርሲቲዎች የሚነሱ የአቅርቦት፣ የብሄር፣ የፖለቲካና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች በበለጠ ለተማሪዎች ቅርብ ስለሆኑ በእኔነት ስሜት ችግሮቹ ጉዳት ሳያደርሱ እንዲፈቱ ካለፈው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ልምድ ያገኙበት መድረክ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸው የመልማት ትልቅ አቅም እንዳለን ማሳያ መሆኑን ጠቁመው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋለው የሠላም ዕጦት ጋር ተያይዞ ሰፊ የትምህርት ጊዜ ሲባክን እንደነበር አውስተዋል፡፡ የሠላም ዕጦቱ የትምህርት ብክነት ከማስከተሉ ባሻገር በሀገራችን ዕድገትም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ለወደፊቱ ሁላችንም ለሠላም ቅድሚያ ሰጥተን በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተማሪዎች ኅብረት የሚጠበቅበትን ድርሻ በኃላፊነትና በባለቤትነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ኦሊ በዳኔ ኅብረቱ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዓመታዊ ጉባዔውን እንዲያካሂድ ለፈቀደውና ላዘጋጀው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናውን አቅርቦ ከኮሮና በኋላ የመማር ማስተማር ሥራ ሲጀመር መሆን ስለሚገባው የኅብረቱና የተማሪዎች ሚና ዙሪያ፣ በዩኒቨርሲቲዎች እየተፈጠሩ የሚገኙ የሠላም መደፍረሶች በሚቀረፉበት ሁኔታ፣ የሀገር አቀፉን ኅብረት ማዋቅር ማሻሻያ ማድረግና በአዘጋጁ ዩኒቨርሲቲ የችግኝ ተከላ በማካሄድ አረንጓዴ አሻራ ማኖር ዋነኞቹ የጉባዔው መርሃ-ግብሮች ነበሩ ብሏል፡፡ በአጀንዳዎቹም ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ በጋራ መግባባት ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡ፣ ለኅብረቱ አመራሮች ቀጣይ ሥራ አጋዥ የሆነ በአመራር ክሂሎትና ዕውቀት ዙሪያ ያተኮረ ሥልጠና መሰጠቱና በአጠቃላይ ለቀጣይ የማኅበሩ ሥራዎች ውጤታማነት የሚረዱ ውሳኔዎችና አቋሞች ተንፀባርቀው ሁላችንንም አደራ የተቀበልንበት ጉባዔ በመሆኑ ቆይታው እጀግ ውጤታማ ነበር ሲል ተማሪ ኦሊ ተናግሯል፡፡

በውይይቱ በኅብረ-ብሔራዊነት፣ መቻቻልና አብሮነት ዙሪያ ያጠነጠነ ጥናታዊ ጽሑፍ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት በዶ/ር ሀብታሙ አበበ ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በጉባዔው የ45ቱም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ኅብረት ፕሬዝደንቶችና ሥራ

አስፈፃሚዎች፣ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የጋሞ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዲላ፣ የዋቸሞና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት