በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል በ‹‹Infectious Diseases›› 3ኛ ዲግሪ እንዲሁም በ ‹‹Bio-Medical Sciences›› 2ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም ለመክፈት የሚያስችለውን የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ ነሐሴ 26/2012 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ባስቀመጠው ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያስፋፋ ሲሆን በዚህም እንደ ሀገር የተሰጠውን ጥራትና ብቃት ያላቸውን ከፍተኛ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎችን ለሀገሪቱ ማበረከቱን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ-ትምህርቶቹ ለውጭ ግምገማ ከመቅረባቸው በፊት የተለያዩ ሂደቶችን ማለፋቸውን የተናገሩት ዶ/ር የቻለ ፕሮግራሞቹ ሌሎች አስፈላጊ ሂደቶችን በተጨማሪ አልፈው ተማሪ በመቀበል የማስተማር ሥራ እንዲጀመር ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ በበኩላቸው ኮሌጁ ፕሮግራሞቹን ለመጀመር የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መቆየቱን ጠቁመው በኮሌጁ ፕሮግራሞቹን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ የሰው ኃይል እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዘርፎቹ የሚመረቁ ተማሪዎችም በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተፈላጊ መሆናቸውን በተደረገው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በማረጋገጥ ሥርዓተ-ትምህርቶቹ አስፈላጊ ሂደቶችን እንዲልያፉ ተደርጎ በ2013 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ማስተማር እንጀምራለን ብለዋል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እያደረጉ ሥርዓተ-ትምህርቶቹን ላዘጋጁ ኮሚቴዎችና የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን በ 21 የ3ኛ፣ በ 99 የ2ኛ እና በ 78 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች በማስተማርና በማሠልጠን አገራዊ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት