በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ<<Public Health Nutrition>> እና በ<<Clinical Bio-Chemistry>> የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ መስከረም 7/2013 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ንጉሴ ታደገ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ እንደ ሀገር ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መሆኑን አስታውሰው መሰል የድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞች መከፈታቸው ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲወጣ ከማድረግ አንፃር ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚከፈቱ አዳዲስና ነባር የትምህርት ፕሮግራሞችን ጥራት ለማረጋገጥም በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ሥርዓተ-ትምህርቶቹ የውስጥ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ሂደቶችን ማለፋቸው ገልፀዋል፡፡ ሁለቱም ፕሮግራሞች ያላቸውን ተገቢነትና የገበያ ፍላጎት ለማወቅ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መደረጉን የጠቆሙት ዶ/ር ታምሩ በሁለቱም የትምህርት መስኮች እንደ ሀገር ከፍተኛ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል ዕጥረት እንዳለ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ለአብነትም እንደ ሀገር ያለን የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች 1600 ብቻ መሆኑ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሞቹ ከዚህ በኋላ የሚቀሩ ሂደቶችን ካለፉ በኋላ ተማሪ በመቀበል የማስተማር ሥራ ይጀመራል ያሉት ዶ/ር ታምሩ ፕሮግራሞቹን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ የሰው ኃይልና የቤተ-ሙከራ ግብዓት በዩኒቨርሲቲው መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ አክለውም የኮሮና ቫይረስ አጠቃላይ ዓለምንና ሀገራችንን እየፈተነ በሚገኝበት ወቅት ከሥርዓተ-ትምህርቶቹ ዝግጅት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ለተሳተፉ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሥርዓተ-ትምህርት ግምገማው ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የመጡ 4 የዘርፉ ምሁራን የተገኙ ሲሆን የሁለቱም ፕሮግራሞች መከፈት እንደ ሀገር በዘርፎቹ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል ዕጥረት ለመቅረፍ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክቱ ገልፀው በሥርዓተ-ትምህርቶቹ ላይ ሊጨመሩና ሊቀነሱ ይገባቸዋል ያሉዋቸውን ነጥቦች አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት