የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር /BFA/ የደቡብ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ‹‹የሥርዓተ ፆታ ግንዛቤ፣ አካታች ጽንሰ ሀሳቦችና ዘዴዎቹ›› በሚል መሪ ቃል በሥራ ክፍሉ ለሚገኙ ባለሙያዎች እና ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ከጥቅምት 09/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት ስሲጥ የነበረው የአሠልጣኞች ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ስምዖን ሽብሩ ሥልጠናው የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሠልጣኞች የሥልጠናውን ውጤት በተግባር እንዲያሳዩና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ የሥልጠናው ዓላማ ሴቶች በግብርና እና በምግብ ዋስትና ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማብቃት እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ʻBFAʼ የደቡብ ፕሮጀክት ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በግብርና ዘርፍ ለሚገኙ ባለሙያዎች በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም በየደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ዲኑ ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት ከብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር /BFA/ የደቡብ ፕሮጀክት ቡድን የመጡት የሥርዓተ ፆታ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉ ብርሃኑ ሥርዓተ ፆታ ማኅበረሰቡ ለሴቶችና ለወንዶች የሚሰጠው የሥራ ክፍፍልና የኃላፊነት ሚና መሆኑን በመግለፅ በሥርዓተ ፆታ ግንዛቤ ክፍተት ምክንያት በሥራ አካባቢና በተለያዩ ሁኔታዎች የሚስተዋሉ የአመለካከትና የአረዳድ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ሠልጣኞች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም ሥልጠናው ሥርዓተ ፆታና ዕድገቱ፣ የሥርዓተ ፆታ ህግና ፖሊሲ፣ በሥራ አካባቢ የጋራ መረዳዳት፣ የመረዳት ችሎታና አተገባበር፣ የሴቶች ማኅበራዊ እሴቶች፣ በተቋሙ ውስጥ የሴቶችን የኃላፊነት ሚና ማሳደግ የሚሉት ትኩረት ከሚደረግባቸው ነጥቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ በቀጣይ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሥርዓተ ፆታ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና እንዲሁም በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ዳይሬክቶሬቱ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር በግብርናው ዘርፍ የወንዶችንና ሴቶችን ተሳትፎ በማሰደግ በምግብ ዋስትናና ምርትና ምርታማነትን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ፆታዊ ጥቃት በተዛባ የሥርዓተ ፆታ ግንዛቤና አስተሳሰብ ምክንያት የሚፈፀም ስለሆነ ችግሩን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሥልጠናው የዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች የሥርዓተ ፆታ አስተባባሪዎች፣ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ሴት መምህራን፣ ከአላጌ እና ከደብረ ዘይት ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከወላይታ ቴክኒክና ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የተወጣጡ የሥርዓተ ፆታ አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት