የኤፌዴሪ ፕሬዝደንት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥቅምት 12/2013 ዓ/ም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተገኙበት ዩኒቨርሲቲው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ እንዲያገኙ ከተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ መንግሥት በተለይም ለሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች ለሚመጡ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች 75 በመቶው ሴቶች እና 25 በመቶው ወንዶች መሆናቸውን ፕሬዝደንቷ ተናግረው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ሴት ተማሪዎች በጥሩ ውጤት ተመርቀው እንዲወጡ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት አድርጎ እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለውን አጭር ታሪክ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በሴት ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ዙሪያ እየሠራ ያለውን ሥራ የተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በፕሮግራሙ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሣ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ክብርት ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የደቡብ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ እርስቱ ይርዳው፣ የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴና ሌሎች የፌዴራል፣ የክልል፣ የጋሞ ዞንና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የጋሞ አባቶች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት