አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጂኦ ስፓሻል ትምህርትና ሥልጠና፣ ምርምር፣ ዕድገት እንዲሁም መረጃ ልውውጥ ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር ቱሉ በሻ እንደገለጹት ተቋሙ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት በሚል ስያሜ ሀገሪቱን ለ74 ዓመታት ያገለገለ፣ አንጋፋና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያለው ሲሆን የጂኦ ስፓሻል መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የማምረት፣ የማከማቸት፣ የማስተዳደርና የማሰራጨት ተልዕኮ የተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መሥራቱ ለዘርፉ ዕድገት የራሱ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ዶ/ር ቱሉ በተለይ ዩኒቨርሲቲው ለዚሁ ዓላማ ያሠራውን ግዙፍ ማዕከል በመጠቀም ማዕከሉ በደቡብ የሀገራችን ክፍል የጂኦ ስፓሻል ትምህርት፣ ሥልጠናና ምርምር እንዲሁም የልኅቀት ማዕከል እንዲሆን እንሠራለን ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢንደስትሪዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተባብረው መሥራታቸው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ፣ በዕውቀትና በክሂሎት የዳበሩና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉ/ም ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያችን እንደ ሀገር ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ አንደመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ለሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የሚያስፈልጉ የጂ.አይ.ኤስ (GIS)፣ የሪሞት ሴንሲንግና በአጠቃላይ የጂኦ ስፓሻል መረጃዎችን ተማሪዎችና መምህራን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ስምምነቱ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ ይህም የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማሳለጡ ባሻገር በዘርፉ የኒቨርሲቲው የልኅቀት ማዕከል እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ለዚሁ ሥራ በከፍተኛ ወጪ አስገንብቶ ያጠናቀቀው የጂኦግራፊና ጂኦ-ኢንፎርማቲክስ ማዕከል አገልግሎት ላይ እንዲውል በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብዓት ለማሟላት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ ኮሌጁ በዘርፉ ከመጀመሪያ እስከ 3ኛ ዲግሪ በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን አስታውሰው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካለው ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር መሥራታችን ተማሪዎቻችን በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ጥራት ያላቸው ምሩቃንን እንድናፈራ ያግዛል ብለዋል፡፡ የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ ውጤታማ እንዲሆንና ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የምርመር፣ የሥልጠናና የመረጃ ማዕከል እንዲሆን ኮሌጃቸውና የኮሌጁ መምህራን ቁርጠኛ መሆናቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት እንደተጠቀሰው ሁለቱ ተቋማት በሰው ኃይል ልውውጥና ሥልጠና፣ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ምርምርና ፕሮጀክቶችን መሥራት፣ የስፓሻል መረጃዎችን መለዋወጥ፣ ከጂኦ ስፓሻል መረጃ ጋር የተያያዙ የትምህርትና

ሥልጠና መስኮችን መክፈት፣ በጂኦ ኢንፎርማቲክስ ቤተ-ሙከራዎች የተግባር ሥልጠና ለተማሪዎችና መምህራን መስጠት፣ የጂኦ ስፓሻል መሠረተ ልማትና ዳታቤዝ መገንባት ላይ በትብብር ይሠራሉ፡፡

የጂኦ ስፓሻል መረጃዎች ወቅታዊ የአየር ላይ ፎቶግራፍ፣ በቅየሳ፣ በካርታ አነሳስ፣ በሪሞት ሴንሲንሲንግና በጂ.አይ.ኤስ ዘዴዎች የሚሰበሰብ፣ የሚቀናበርና ለተጠቃሚዎች የሚቀርብ ከጂኦግራፊያዊ ማጠቃሻ ጋር የተዛመደ መረጃ ሲሆን በመሬት ላይ ለሚከናወኑ የመንገድና ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች፣ የከተማ ማስተር ፕላን ዝግጅት፣ ለዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት ዝርጋታ፣ ለግድቦች ግንባታ፣ ለማዕድን ፍለጋ ወዘተ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን በትምህርት ክፍሉ የጂ.አይ ኤስና ሪሞት ሴንሲንግ መምህር አቶ ደንበል ጎንታ ተናግረዋል፡፡

ከስምምነቱ ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የመጣው ልዑክ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ያስገነባውን የጂኦግራፊና ጂኦ ኢንፎርማቲክስ ማዕከልና የአይሲቲ (ICT) መሠረተ ልማቶችን የጎበኘ ሲሆን የልዑኩ አባላት ዩኒቨርሲቲው ለመስኩ የሰጠውን ትኩረት ከጉብኝቱ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት