በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መማር ማስተማርን ለማስቀጠል ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በቀረበው የመተዳደሪያ መመሪያ ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ጥቅምት 20/2013 ዓ/ም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራን ለማስቀጠልና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመተዳደሪያ መመሪያ መኖሩ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ መምህራን፣ አስተዳደር ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች በግቢ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት መመሪያውን በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲያደርጉ ዶ/ር ዳምጠው አሳስበዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ሕግ/አገ/ዳይ/ዳይሬክተር አቶ መርኪያ መንገሻ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባል ኮቪድ-19 እንዳለበት እያወቀ ከለይቶ ማቆያ አምልጦ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባት፣ ከተቋሙ ማኅበረሰብ ጋር መቀላቀል፣ ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ከትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብ አባላት ጋር መገናኘት፣ በእጅ መጨባበጥ፣ አካላዊ ንክኪ ማድረግ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርግ መንቀሳቀስ በፍፁም የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡ መመሪያው መብቶችን፣ የተከለከሉ ተግባራትንና የተጣሉ ግዴታዎችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን በተጨማሪም ከአነስተኛ እስከ በጣም ከፍተኛ ጥፋቶችንና የሚያስከትሉ የቅጣት ዓይነቶችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም በመመሪያው የተዘረዘሩትን ግዴታዎች አለማክበር ለተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ እስከ መሰናበት፣ ለመምህራን ከሥራ ገበታ ሙሉ በሙሉ እስከ መሰናበትና እስከ 3 ዓመት በየትኛውም የትምህርትና ሥልጠና ተቋም ውስጥ በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት ቅጥር መፈጸም እስከ አለመቻል፣ ለአስተዳደር ሠራተኞች ከሥራ ገበታ ሙሉ በሙሉ እስከ መሰናበት እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ከሥራ ገበታ ሙሉ በሙሉ እስከ መሰናበትና አግባብነት ባለው ሕግ እስከ መጠየቅ ድረስ የሚያደርስ ቅጣት የሚያስከትል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መመሪያው ጥቅምት 16/2013 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት ቀርቦ በተቋም ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምዕ የፀደቀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት የሥራው ባለቤት ሆኖ የዩኒቨርሲቲው አስ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ የየካምፓስ ዲኖችና የፋከልቲና ት/ክፍል ኃላፊዎች በተዋረድ የመመሪያው አስፈፃሚዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት