የዩኒቨርሲቲዉ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች መምህራን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዋናዉ ግቢ አቅራቢያ ከሚገኙ ሦስት ቀበሌያት ለተወጣጡ 100 ተማሪዎች የመማሪያ ደብተርና እስክሪፕቶ ድጋፍ ጥቅምት 19/2013 ዓ.ም አድርጓል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በኮቨድ-19 ምክንያት ተዘግተዉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ሲከፊቱ ተማሪዎች የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸዉን ከኮቪድ-19 እየጠበቁ ትምህርታቸዉን ጠንክረው እንዲማሩ መክረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረስብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት ወጥተዉ መሥራት ላልቻሉ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ማዕድ በማጋራት የምግብ ጥሬ ዕቃ፣ የንጽህና መጠበቅያ፣ የአልባሳት ድጋፍ እንዲሁም ከፍተኛ ችግር ላለባቸው ቤተሰቦችም ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የመኖሪያ ቤት ገንብቶ መስጠት የመሳሰሉትን የበጎ አድራጎት ሥራዎች እየሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የውሃ ተክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ድጋፉ በአቅም ውስንነት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ እንዳያቋርጡ ለማድረግ ያለመ ሲሆን ለዚህም የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች መምህራን አርባ ስድስት ሺ ብር አዋጥተዋል ብለዋል፡፡

በዓባያ ክፍለ ከተማ የልማት ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ኦይቸና በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር በመረዳት ይህንን ድጋፍ በማድረጉ በቀበሌዉ ማኅረሰብ ስም ምሥጋናቸውን አቅርበው ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መሰል ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ መምህራን የምስጋናና የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት