የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሠረት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአማካሪ ምክር ቤት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ተቋቁሟል፡፡

የአማካሪ ም/ቤቱ የጋሞ ዞን አስተዳደር፣ የጋሞ ዞን ደኅንነትና ፀጥታ ኃላፊ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና የአስ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት፣ የጋሞ ዞን የውሃ፣ የመብራት ኃይልና የቴሌኮም አገልግሎት ኃላፊዎች፣ የሐይማኖት ተቋማት ኅብረት ሰብሳቢና የየቤተ እምነቱ ተወካዮች፣ የጋሞ አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የአከባቢው ወጣቶች ተወካዮችን ያካተተ ሲሆን በመጀመሪያ ስበሰባው አባላቱ በተገኙበት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የአማካሪ ምክር ቤቱ ዓላማ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በላቀ ደረጃ እንዲወጡ የአከባቢውን ማኅበረሰብ በንቃት በማሳተፍ የተረጋጋና ሠለማዊ የመማር ማስተማር አከባቢን መፍጠር ነው፡፡

የጋሞ ዞን ምክትል ዋ/አስተዳደሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደገለጹት የአማካሪ ም/ቤቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ተልዕኮ የሆነው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ በሠላማዊ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በሰነዱ እንደተብራራው በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የአማካሪ ምክር ቤት ማደራጀት አስፈላጊነቱ ተቋማት ለአከባቢው ማኅበረሰብ የሚሰጡትን አገልግሎት አግባቢነት፣ ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል፣ በተቋማቱ እና በአከባቢው ማኅበረሰብ መካከል ተከታታይነት ያለውና መደበኛ የግንኙነት መድረክ በመፍጠር ከተቋሙ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ሳይፈጠሩ ለመከላከልና ሲፈጠሩም በአጭሩ ለመቅጨት በጋራ ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ፣ ማንኛውም በተቋማቱ ውስጥና ዙሪያ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች በተቋማቱም ሆነ በአከባቢው ማኅበረሰብ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ፣ ተቋማቱ ለአከባቢውና ለሀገር ያበረከቱትንና እያበረከቱ ያለውን አስተዋፅዖ በተገቢው ሁኔታ ለማስተዋወቅ፣ ለቀጣይ ጊዜያት የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ገንቢ ግብረ መልስ ለማስገኘትና ተቋማቱ በሚኖራቸው የተራዘመ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባሮቻቸው በአከባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የባለቤትነት ስሜትን ለማጎልበት ምቹ ማዕቀፍ ለመፍጠር  ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት