የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ የንጽህና መጠበቂያዎች አመራረት ሂደትን አስመልክቶ ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም ጉብኝት አካሂደዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ወደ ማኅበረሰቡ በማሸጋገር የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየሠራ ነው፡፡ ከዚህም አንፃር ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 39 የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ከምርምርና የፈጠራ ሥራዎቹ መካከልም በኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራ እየተዘጋጀ የሚገኘው የንጽህና መጠበቂያዎችን የማምረት ሂደት ይገኝበታል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ፀጋዬ ፈቃዱ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የንጽህና መጠበቂያዎች ፍላጎትና አቅርቦት ተመጣጣኝ ያለመሆኑና በገበያ ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ፕሮጀክቱን ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡ ምርቱ በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ዕጽዋትና ሌሎች ፀረ-ተህዋስያንን በመጠቀም የሚዘጋጅ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው ይህም ዋጋውን ተመጣጣኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው ሂደትም 4 መቶ ሺ ሚሊ ሊትር የንጽህና መጠበቂያ ማዘጋጀት የተቻለ ሲሆን በቀጣይም ለሥራ አጥ ወጣቶች አጫጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለመስጠት ማኑዋሎች እየተዘጋጁ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ይህም ወጣቶቹ እንዲችሉና የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው ይረዳል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት