የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ኢኖቬቲቭ እንሰት ሪሰርች ፕሮጀክት›› የእንሰት ምርት ሂደትን የሚያግዙ ማሽኖችን በቴክኖሎጂና በፈጠራ በመሥራት የዩኒቨርሲቲው፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ኅዳር 29/2013 ዓ/ም ለማኅበረሰቡ አስተዋውቋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹ኢኖቬቲቭ እንሰት ሪሰርች ፕሮጀክት›› የእንሰት ምርት ሂደትን በቴክኖሎጂና በፈጠራ ለማገዝ እንዲቻል ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ጥር/2012 ዓ/ም ይፋ ያደረገው ፕሮጀክት መሆኑን በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለ3 ዓመታት የሚቆይና የእንሰት ምርት አዘገጃጀት ሂደትን የሚያፋጥኑ፣ የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡና የምርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ምርምሮችን ለማካሄድና ማሽኖችን አዘጋጅቶ ለማዳረስ ያለመ ሲሆን ለሥራው ማስፈፀሚያ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 4 ሚሊየን ብር መመደቡን ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

እንሰትን የማብላላት ሂደት (Fermentation) ከ2-3 ወራትን እንደሚፈጅ የሚናገሩት ዶ/ር አዲሱ እንሰቱን ከመቁረጥ እስከ ማብላላት ያለው ሂደት በባህላዊ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ በተለይም የሴቶችን ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ የሚጠይቅ፣ ለድካምና ለተለያዩ ህመሞች የሚያጋልጥ እንዲሁም የምርት ጥራት ችግርና ብክነት የሚያስከትል ነው፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍና ሂደቱን በፈጠራ ለመደገፍ የእንሰት መቁረጫ፣ መፋቂያ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማሽኖቹ በዩኒቨርሲቲው ሜካኒካል ወርክሾፕ የተሠሩ ሲሆን በሌሎች ሀገራት ጥቅል ጎመንን ለማብላላት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ በማምጣት ለቆጮ ማብላያና ማስቀመጫነት እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ማስቀመጫዎቹን በአካባቢው በቀላሉ በሚገኙ የሸክላና ፕላስቲክ ቁሳቁሶች ለመተካትም እየተሠራ ነው፡፡

ከተሠሩት ማሽኖች መካከል የእንሰት ሥር (ሀምቾ) መቁረጫውና የቆጮ መጭመቂያው በቀላሉ በእጅ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ የእንሰቱን ግንድ በመፋቅ ቆጮውን ከቃጫው የሚለየው እንዲሁም በእጅ የተቆራረጠውን ሀምቾ የሚፈጨው ማሽን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማሽኖቹና የማብላያ ማድጋዎቹ የእንሰት ምርትን ለማዘጋጀት የሚጠይቀውን ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ በእጅጉ የሚቀንሱ ከመሆናቸው ባሻገር እንሰት በባህላዊ መንገድ ሲዘጋጅ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠረውን ተፈጥሯዊ ጣዕም የማጣት፣ መጥፎ ጠረን የመፍጠር፣ የመጥቆርና የምርት ብክነት ችግሮች ያስቀራሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ማሽኖቹን የማላመድ ሂደቱን ክትትል በማድረግ ከ3 ወራት በኋላ በሚሰበሰበው ግብረ መልስ መሠረት የቴክኖሎጂውን ጉድለቶች በመለየት አስፈላጊ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ፡፡ ቴክኖሎጂው የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረሱ ሲረጋገጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ በማባዛት በሀገሪቱ እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለማዳረስ ይሠራል፡፡

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ ተቋማት ተሠርተው ወደ ማኅበረሰቡ ሊወርዱ የሚገባቸውን ምርምሮች በገንዘብ የሚደግፍ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ የአርባ ምንጭ

ዩኒቨርሲቲ ኢኖቬቲቭ እንሰት ሪሰርች ፕሮጀክትም የዚሁ አካል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በታየው ተስፋ ሰጪ ውጤት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በፕሮቶታይፕ ደረጃ ያለውን ሥራ በማስፋፋት በቀጣይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጋሞ ደጋማ አካባቢዎችና በሌሎችም እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምርታማነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ዓለሙ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከንድፈ ሃሳብ ተሻግሮ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለውጤት በመብቃቱ ለሌሎች አካባቢዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ሞዴል መሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በስፋት ለማስተዋወቅ፣ ለመደገፍና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዳረስ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉና ለቀጣይ ሥራዎች ከዩኒቨርሲቲው፣ ከተመራማሪዎቹና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ በዶርዜ ሆሎኦና በግርጫ የሙከራ ጣቢያዎች በመገኘት ባህላዊው የእንሰት ምርት አዘገጃጀት፣ የምርምር ውጤቶችና በፕሮጀክቱ የተሠሩ ማሽኖች የተጎበኙ ሲሆን ከፕሮጀክቱ ጋር በቅርበት ከሚሠሩ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት በማካሄድ በቀጣይ ሥራዎችና ማሻሻያዎች ላይ አስተያየት ተሰብስቧል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮች ባህላዊው የእንሰት ምርት አዘገጃጀት እጅግ አድካሚና ጊዜ የሚወስድ እንዲሁም ተፍቆ በጉድጓድ ውስጥ ሲቆይ የሚጠቁርና መጥፎ ጠረን የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማሽኖቹ ተሠርተው ለሙከራ በመቅረባቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸው ማሽኖቹን በሚሞክሩበት ጊዜ ያስተዋሏቸውንና ቢሻሻሉ ያሏቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ-ሙከራዎችን በመጎብኘት በቤተ-ሙከራዎቹ የተሠሩ ቴክኖሎጂዎችን ተመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የጋራ ስምምነት አድርጎ በሚሠራቸው ቀጣይ ሥራዎች ላይም ውይይት ተካሂዷል፡፡

ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት