ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ከሚደርስባቸው አደጋ ለመከላከል በዩኒቨርሲቲው በተጠናው ጥናት መሠረት አቅጣጫውን በመሳት የሚመጣውን የዝናብ ውሃ መከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ወደ ተግባር ለማስገባት የካቲት 03/2013 ዓ.ም ሰነድ ቀርቦ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሰነዱ በጫሞ ሐይቅ ውስጥ ባለው ብዝሃ ህይወት ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከልና መልሶ ማገገም በሚያስችሉ ጉዳዮች፣ የሐይቁን የተፋሰስና የውሃ ፍሰት ከመቆጣጠር አኳያ የሚሠሩ ሥራዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጥናትና ማኅበረሰቡ የሚጠቀመው የደን ውጤቶች በነጭ ሳር ፓርክና በውስጡ በሚኖሩት እንስሳት ላይ እያደረሰ ባለው አሉታዊ ተጽዕኖ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የሰነዱ አቅራቢና የፕሮጀክቱ ም/ሰብሳቢ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት በፕሮጀክቱ በዋናነት ኩልፎ ወንዝ አቅጣጫውን ይዞ እንዲሄድ የሚያደርግና ደለልና ሌሎች ነገሮችን በማጣራት ውሃውን የሚለቅ የአጥርና የእርከን ሥራ እንዲሁም በፓርኩ ዙሪያ የአጥር ሥራ የሚሠራ ሲሆን ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ የአጭር ጊዜ ዕቅድ ተይዞ የሚሠራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከኩልፎ ወንዝ በመቀጠል እንደየደረጃቸው በጫሞ ተፋሰስ አካባቢ ያሉትን ሲሌ፣ ወዘቃና ሌሎች ወንዞችን የተፋሰስ ሥራ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት የሚያከናውን ይሆናል፡፡

ተፋሰሱን ለጉዳት የሚያጋልጡ የአስተራረስ ሁኔታዎችና ከዚህ ቀደም የማይታረሱ ገደላማና ተዳፋት ቦታዎች በመታረሳቸው ደኖች በቀላሉ ተሸርሽረው እንዲጠፉ ምክንያት እንደሆነ እንዲሁም ተፋሰሱ በምን ሁኔታ ቢሠራበት አፈርና ውሃን መጠበቅ እንደሚቻል በሰነዱ ተጠቅሷል፡፡

ከተያዘው ፕሮጀክት ሥራ በተጨማሪ በጫሞ ተፋሰስና በፓርኩ ዙሪያና በአካባቢው ያለው አፈር ተጠርጎ እንዳይመጣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መሥራት፣ ቀርከሃና መሰል ዕጽዋትን በመትከል አፈርና ውሃን እንዲይዙ ማድረግ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ማመቻቸትና የማገዶና የደን ውጤቶች በከተማው አስተዳደር ወጥ የሆነ የመገበያያ ስፍራ ማዘጋጀት ለችግሮቹ ከተቀመጡ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል ናቸው፡፡

ለፕሮጀክቱ ከታቀደው በጀት በተጨማሪ የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር በኃ/ማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን አስተባባሪነት ሌሎች ድጋፎችን ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት በማሰባሰብና የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕሮጀክቱ ሥራ እንደሚጀመር ተጠቁሟል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በሀገር አቀፍና በዞን ደረጃ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክን ለማዳን የተጀመረው እንቅስቃሴ አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው ፓርኩን በፍጥነት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ለማከናውን ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ም/ዋ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ብዙ ጥናቶች ተሠርተው ወደ ተግባር ባለመግባታችንና በትብብር መሥራት ባለመቻላችን ችግሮች እየተባባሱ መጥተዋል ብለዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሞ ጎዴቦ ፓርኩን ብሎም ሁለቱን ሐይቆች ለመታደግ የተጀመረው ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብረው በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ከጋሞ ዞን አስተዳደር፣ ከዞኑ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር፣ ከዞን ፖሊስ፣ ፍትህና ጸጥታ፣ ከዞን ግብርና መምሪያ፣ ከክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ የተወጣጡ ተሳታፊዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት