ላለፉት 2 ዓመታት በ5 ክልሎች በሚገኙ 62 ወረዳዎች የሴፍቲኔት ተረጂ አርሶ አደሮችን ማዕከል በማድረግ ሲሠራ የቆየው የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ሥራዎችን ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የመንግሥት አካላት በራስ አቅም ማስቀጠል እንዳለባቸው ከየካቲት 19-20/2013 ዓ/ም ሀዋሳ ላይ በተደረገው የፕሮግራሙ ክልላዊ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ሀገር አቀፍ አስተባባሪ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ ፕሮግራሙ እንደ ሀገር ከሚገኙ 350 የሴፍቲኔት ወረዳዎች መካከል በ62ቱ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ፕሮግራሙ በዋናነት በአካባቢዎቹ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥነ-ምግብ /nutrition/ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ሲሰጥና የእንሰት መፋቂያ፣ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የዶሮ ማርቢያ ወዘተ ቴክኖሎጂዎችን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ ፕሮግራሙ በቆይታው እንደ ሀገር 230 ሺህ ቤተሰቦችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ማድረጉን ዶ/ር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የፕሮግራሙ አማካሪ ም/ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር አያኖ ባሪሶ ፕሮግራሙ በደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሀዋሳና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በ10 ወረዳዎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ምርታማነትን ከ50-100 በመቶ ማሳደግ የቻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ፣ የማላመድ፣ የማሰራጨት ውጤታማ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በፕሮግራሙ የተገኙ ልምዶችን ማስፋት ይገባል ያሉት ዶ/ር አያኖ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሥራውን ተረክበው ሊያስቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ በመድረኩ በፕሮግራሙ በ2 ዓመታት ውስጥ የተሠሩ ሥራዎችን ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸውም በፕሮጀክቱ የተዋወቁ ውጤታማና ምርትና ምርታማነትን፣ የምግብ ዋስትናን እንዲሁም የሥነ-ምግብ ሥርዓትን ማሻሻል የሚያስችሉ የጥራጥሬ፣ የፍራፍሬና የጓሮ አትክልትን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ዝርያዎችንና አሠራሮችን ለአርሶ አደሩ በስፋት ማስተዋወቅ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፕሮግራሙ በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ዶ/ር መብራቱ ፕሮግራሙ የሥራ ጊዜውን እያጠናቀቀ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሥራውን በባለቤትነት ወስደው ሊያስቀጥሉ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በበኩላቸው በቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረው ሥራውን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኮሌጃቸው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሥራው ሂደት ለመሳተፍ በቂ የሆነ የሰው ኃይል መኖሩንና ሥራው በቁርጠኝነት ከተሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመዝጊያ ንግግራቸው የፕሮጀከቱን ሥራዎች የማስቀጠል ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አሳስበው የቀጣይነት ዕጣ ፋንታው በእኛው እጅ ላይ ነው ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የ2 ዓመታት ቆይታ በርካታ ልምድና አቅም እንዲሁም ትስስር መፍጠር እንደተቻለ የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ከዚህም በመነሳት ፕሮጀክቱን በራስ አቅም ማስቀጠል ይቻላል የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሁላችንም በትብብር መሥራት አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት