አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 8ኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ግምገማ ከየካቲት 26-27/2013 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው የጥናትና ምርምር ሥራ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለመጠቆም እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ የምርምር ሥራዎች መበራከት የሚበረታታ በመሆኑ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ምርምሮችን መሥራት የመጀመሪያ ምርጫ መሆን አለበት ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የጥናትና ምርምር ግምገማ መድረክ በምርምር ሂደት ላይ ያሉና የተጠናቀቁ የጥናት ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና ውጤታማነታቸውን ለመገምገም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የጥናትና ምርምር ቤተ-ሙከራዎችን ማደራጀትና በግብዓት ማሟላት አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም የትምህርትና የምርምር ጆርናሎችንም የማዘጋጀት ሥራ በትኩረት እንደሚከናወንና ይህንንም በአግባቡ ለማስፈጸም የምርምር መዋቅሮችን በማጥናት ማሻሻያ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ተሠርተው የተጠናቀቁ 68 ምርምሮች የቀረቡ ሲሆን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው ከመድረኩ በተሰጡ ሳይንሳዊ አስተያየቶች መሠረት የተሟላ ምርምር እንዲሆኑ በማድረግ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ ይሠራል ብለዋል፡፡

‹‹የኩልፎ ወንዝ የውሃ ጥራት ምዘናና የብክለት መንስኤዎችን መለየት››፣ ‹‹በከተሞች ያልታከመ ውሃና የደለል ፍሰት››፣ ‹‹የጫሞ ሐይቅ በኩልፎ፣ ሲሌና ኤልጎ ወንዞች መበከል››፣ ‹‹የሀሬ፣ ሻፌ እና ባሶ ወንዞች የዓባያ ሐይቅን መበከል››፣ ‹‹የሰብሎችና የዕፅዋት እድገት›› እንዲሁም ‹‹በአልኮል መጠጥ የሄፐታይተስ ቢ ቫይረስ ኢንፌክሽን›› ከቀረቡ ጥናቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ አስተባባሪዎች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በጥናትና ምርምር ግምገማ መድረኩ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት