የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በእጅ የሚሠራ ቀላል የኦቾሎኒ መፈልፈያ ማሽን አዘጋጅቶ በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ ኦቾሎኒ አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች ለሙከራ በማቅረብ አጠቃቀሙን አስመልክቶ የካቲት 24/2013 ዓ.ም በሰላምበር ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በመክፈቻ ንግግራቸው ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዋና መሠረት የሆነውን ግብርና አዘምኖ ወደፊት ማስቀጠል መንግሥት ከያዘዉ የእድገት አቅጣጫ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን ለማሳደግ የግብርና ሥራዎች ጊዜን የሚቆጥቡ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩና ኢኮኖሚን የሚያዳብሩ እንዲሆኑ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ከዚህ ቀደም የወተት መናጫና የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ለአርሶ አደሩ ማቅረባቸውን አስታውሰው አካባቢው በጋሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች በኦቾሎኒ ምርት ታዋቂ በመሆኑ ለአጠቃቀም ቀላልና ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን ቆጣቢ የኦቾሎኒ መፈልፈያ ማሽን ለሙከራ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዕጽዋት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ዘነበ መኮንን እንደገለጹት የኦቾሎኒ ምርት ለዘይትና ለተለያዩ ቅባቶች ማምረቻ ግብዓት የሚውል ሲሆን የዘይት ተረፈ ምርቱ (ፋጉሎ) ለከብት መኖነት ያገለግላል፡፡ የኦቾሎኒ ምርትን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ተግባራት አንዱ የመፈልፈል ሂደቱ ነው ያሉት ዶ/ር ዘነበ በዚህ ሥራ በአብዛኛው የሚሳተፉትና የችግሩ ገፈት ቀማሾች ሴቶች ናቸው፡፡ በሂደቱ 10 ኪ.ግ ለመፈልፈል በበርካታ የሰው ኃይል 1 ቀን ሙሉ የሚፈጅ ሲሆን ሥራው አሰልቺና በብዛት ሲፈለፈል የእጅ ጣቶችን በማቁሰል ጤናቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ ለሙከራ የቀረበው ማሽን በአማካይ በ1 ሰዓት 22.5 ኪ.ግ ለመፈልፈል የሚያስችልና ሲበጠር 17 ኪ.ግ ንጹህ የኦቾሎኒ ምርት የሚያስገኝ ነው፡፡ ይህም የምርት ጥራትን ከማስጠበቅ ማሻገር የአርሶ አደሩን የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ብክነት የሚቀንስና ጤናቸውንም የሚያስጠብቅ ነው፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በኩላቸው የኦቾሎኒ መፈልፈያ ማሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሸሎ የቀረበ መሆኑን ተናግረው ከ3 ወራት የሙከራ ጊዜ በኋላ ከቀረቡት 4 ዓይነት ማሽኖች በአርሶ አደሩ ተገምግሞ የተመረጠውና በዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ተረጋግጦ ኦቾሎኒ አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች የማስተዋወቅና የማላመድ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

ከቁጫ ወረዳ አምቤ ቀበሌ የመጡት አርሶ አደር አቶ ዮሐንስ ዱማ በአካባቢው ታዋቂ የኦቾሎኒ አምራች ቢሆኑም ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ሲፈለፈል የጥራት ችግር እየገጠማቸው ገበያ ላይ ተቀባይነት ማጣታቸውንና በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማሽኑን በማቅረቡ መደሰታቸውን ገልጸው ከሥልጠናው ባገኙት ክሂሎት በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት