አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የእንሰት ምርት ሂደትን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየሠራ ያለው ሥራ አበረታችና ሊሰፋ የሚገባው መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ተናገሩ፡፡ በምክር ቤቱ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዩኒቨርሲቲውና በኢንስቲትዩቱ በኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት አማካኝነት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ከየካቲት 27-28/2013 ዓ/ም በመስክ በመገኘት ምልከታ አድርገዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከመስክ ምልከታው በኋላ በነበረው አጭር ውይይት ወቅት በሰጡት አስተያየት በፕሮጀክቱ እየተሠራ ያለው ሥራ የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ መሆን አለባቸው የሚለውን የምርምር መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ወደ ተግባር የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጅምር ሥራው ከሰፋና በትክክል ተግባራዊ ከተደረገ የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና፣ የሥነ-ምግብና የኢኮኖሚ ችግር ይፈታል ያሉት አባላቱ ቴክኖሎጂዎቹ በስፋት ተመርተው በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ እንሰት አምራች አካባቢዎች የሚዳረሱበት ሁኔታ ላይ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ በማሳተፍ በትብብር መሥራት ይገባል ሲሉ አባላቱ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በመቀበል የጀመርናቸውን ሥራዎች ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ እንደ ሀገር ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ 24 ፕሮጀክቶች መካከል የተሻለ አፈፃፀም እያሳዩ ካሉ ፕሮጀክቶች መካካል ዋነኛው እንሰት ላይ የምንሠራው ፕሮጀክት ነው ያሉት ዶ/ር ካሳሁን ለዚህም ስኬት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የዘርፉ ምሁራን ድርሻ ጉልህ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም የትብብር አድማሳችንን በማስፋት የእንሰት አመራረት ሂደትን የሚያዘምን ብሎም የአምራች አርሶ አደሮችን ሕይወት በተጨባጭ መቀየር የሚያስችል ለውጥ ለማምጣት እንሠራለን ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው አባላት የተሰጡ አስተያየቶች ለቀጣይ ሥራ አጋዥና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ጠቋሚ ናቸው ብለዋል፡፡ የእንሰት ምርምርና ሥርጸት አንዱ የዩኒቨርሲቲው የልኅቀት ማዕከል እንዲሆን የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ፕሮጀክቱ እስካሁን ባለው የሥራ እንቅስቃሴ የእንሰት እርሾና መፋቂያ ማሽኖችን በማምረት ለአርሶ አደሩ ሲያስተዋውቅ መቆየቱን እንዲሁም እንሰትን ለማብላላት የሚሆን እንስራ በአካባቢው ከሚገኙ ቁሳቁሶች በብዛት ማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ፕሮጀክቱ ያገኛቸውን ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎች በማስፋትና በብዛት በማዘጋጀት በሌሎች እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ጭምር በመንቀሳቀስ ለማስተዋወቅ እንደሚሠራ ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

ኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራና ለ3 ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት