125ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ‹‹ዓድዋ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ዓርማ›› በሚል መሪ ቃል በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በሰላም ሚኒስቴር አማካኝነት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በመምጣት ለ45 ቀናት በማኅበረሰብ አቀፍ የበጎ አገልግሎት ሥልጠና ላይ የቆዩ ወጣቶች ሽኝትም ተካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በሌሎችም መገለጫዎች ሳይለያዩ በአንድነት፣ በከፍተኛ የሀገር ተቆርቋሪነትና ጽናት በዘመናዊ ጦር የታገዘና ጡንቻው የፈረጠመውን የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ድል በመንሳት ለሀገርና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነ ድል ማስመዝገብ መቻላቸው በበዓሉ በሰፊው ተዳሷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ባሳዩት ተጋድሎና ባስመዘገቡት ድል ሀገራችን ኢትዮጵያ ድንበሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቃ በመቆየት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆን መቻሏን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ያለን ኢትዮጵያውያን ካለፉት ጀግኖች አርበኞች የሚጠቅመንን ትምህርት በመውሰድ አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር፣ የዕውቀት አድማሳችንን በማስፋትና የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በአግባቡ በመጠቀም ሀገራችንን ላቅ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ገመዳ በበኩላቸው የዓድዋ ድል ነጮች ለጥቁሮች ያላቸውን የበታችነት ዕይታ የቀየረና ለባርነት አገዛዝ ዳግም ፊታቸውን ወደ አፍሪካ እንዳያዞሩ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ክፍል መ/ር የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ በዕለቱ ባቀረቡት ሰነድ የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነውን የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ይዘት፣ በጦርነቱ የኢትዮጵያውያንን ተጋድሎ፣ በዓድዋ ዘመቻ የተንጸባረቁ የትብብር መገለጫዎችንና በጦርነቱ የተሳተፉ ሴት ዘማቾች የነበራቸውን ሚና በዝርዝር ዳስሰዋል፡፡

የብሔራዊ ማኅበረሰብ አቀፍ የበጎ አገልግሎት ሠልጣኞች የሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪ ወ/ሮ ሠናይት አቤልነህ ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት የበጎ አገልግሎት ሠልጣኞች የዓድዋ ድልንና የአርበኞችን ሕይወት እንደ ተሞክሮ በመውሰድ የሀገርን ሰላም በማስጠበቅና ለሀገር ጥቅም የሚቆም ትውልድ በማፍራት ሂደት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ፣ በሰላም ሚኒስቴር የሥልጠና አስተባባሪ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በዓሉን ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት