የፎረሙ ውይይት በዋናው ግቢ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ሚያዝያ 30 ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ኮንፈረንሱን በንግግር በከፈቱበት ወቅት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የፎረሙ ተሳታፊዎች ከመልካም አስተዳደርና ከትምህርት ጥራት አንፃር መሻሻል የሚገባቸውን አፈጻጻሞች በተመለከተ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ በሚያስችል መልኩ ውይይቱን እንዲያካሂዱ አሳስበዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በትምህርት ክፍሎችና በኮሌጆች ደረጃ በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች ተለይተው የወጡ ችግሮችንና ድክመቶችን እንደየባህሪያቸው የአጭር፣ የመካካለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት በዘላቂነት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የሁሉንም ኮሌጆችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ሪፖርቱን ተከትሎ የሁሉም ኮሌጆች ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች አስተያየቶችን፣ ጥቆማዎችንና ጥያቄዎችን በመሰንዘር የመብራት፣ የኢንተርኔት፣ የውሃና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች አካባቢ የሚታዩትን ክፍተቶችና ከፍተኛ መሻሻሎች ገምግመዋል፡፡

ዲኖቹ ለአስተያየትና ጥቆማ ሰጪዎች ምስጋና በመቸር ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሠጡበት ወቅት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መምህራን የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መደረጉን፣ የብቃት ችግር አለባቸው የተባሉ የአንዳንድ የውጭ አገር መምህራን ኮንትራት መቋረጡን እንዲሁም መምህራን የተማሪዎችን ፈተና በወቅቱ አርመው ውጤታቸውን የሚያሳዩበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የ1 5 አደረጃጀት በሁሉም ክፍሎች ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የሚያስችልና ክትትል የሚያደርግ ከአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከመምህራንና ከተማሪዎች የተወከለ የሱፐርቪዢን ቡድን ተቋቁሞ ሥራ ላይ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

የሁሉም ኮሌጆች ዲኖች እንደተናገሩት ከተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ከአስተዳደር ሠራተኞች የስኬት ማነቆ ሆነው የተለዩትን ችግሮች ለመቅረፍ በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊፈቱ የታቀዱ ችግሮችን በተቀናጀ ጥረት ለመሻገር በርትተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

/ር ፈለቀ ኮንፈረንሱን ሲያጠቃልሉ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊተገበሩ የታቀዱ እንዲሁም እስከአሁን መፍትሔ ያልተሰጣቸው የተወሰኑ የአጭር ጊዜ ተግባራት በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራባቸው በመግለጽ የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታን ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡