የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሚያዝያ 16/2007 .ም በሁሉም ካምፓሶች በተደረገው የጧፍ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት በሊቢያ በ30 ኢትዮጵያውያን ላይ ISIS በተባለ አሸባሪ ቡድን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በ4 ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ግድያ በጥብቅ አውግዟል፡፡

በዋናው ግቢ በህሊና ፀሎት የተጀመረውን ሥነ-ሥርዓት በከፈቱበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደተናገሩት በሁለቱም ሀገራት በዜጎቻችን ላይ የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊና አሰቃቂ ግድያ የኢትዮጵያውያንን ልብ በሐዘን የሰበረና በከፍተኛ ሁኔታ ቁጣ የቀሰቀሰ ነው፡፡ ፕሬዝደንቱ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ የምታደርገው የዴሞክራሲ ግንባታና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሸባሪዎች ዕኩይ ዓላማቸውን ለመፈፀም በሚያቀርቡት ሃይማኖታዊ ሽፋን ሳንደናገር የፀረ ሽብርተኝነት አቋማችን ምንግዜም የፀና መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡

በሌሎቹም ግቢዎች የፕሬዝደንት ተወካዮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተወካዮች ለተጎጂ ወገኖች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ መንግሥት ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ ከጎን በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በተለይም የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንትና ተወካዮቹ በሀገራችን ሠርተን የመሻሻል አማራጮች በርካታ ስለሆኑ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር በመውጣት የአሸባሪዎች ሲሣይ መሆን ሊያበቃ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሽብርተኝነትን ከመታገል ጎን ለጎን ወጣቶች በሀገር ውስጥ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ አማራጮችን አሟጠው እንዲጠቀሙና በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሽብር ድርጊቱን የሚያወግዙ የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ የሥነ-ሥርዓቱ ተካፋዮችም ‹‹አክራሪነትና ሽብርተኝነት የትኛውንም ኃይማኖት አይወክልም››፣ ‹‹አንድነታችንን አጠናክረን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን››፣ ‹‹የአይኤስአይኤስ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን በጥብቅ እናወግዛለን›› የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በመያዝና በጋራ ድምጽ በማሰማት ጧፍ እያበሩ በየግቢው በተዘጋጁ ቦታዎች የጥቃቱ ሰለባዎችን በማሰብ የእግር ጉዞ አድርገዋል::