የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ‹‹ዎተርሉ ሃይድሮ-ጂኦሎጂክ›› ከተባለ ካናዳ ከሚገኝ ድርጅት ጋር በመተባበር Environmental and Ground Water Modeling Using Software’ በሚል ርዕስ ከሚያዝያ 26 እስከ ግንቦት 7 ለተከታታይ 11 ቀናት ሥልጠና ተሰጠ፡፡ በሥልጠናው ከአርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ እና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከደቡብ ክልል ውኃ ቢሮ በአጠቃላይ 29 ሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ ሠልጣኞቹ በሥነ-ምድር ሣይንስ እና ሚቲዮሮሎጂ ዲፓርትመንቶች የማስተማር፣ የምርምርና ተዛማጅ ልምድ ያላቸው መምህራንና ሠራተኞች ናቸው፡፡

አሠልጣኝ ሚስተር ዳንኤል ጎምስ እንደተናገሩት ሥልጠናው የተሳታፊዎችን የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን ለመተንተን እና ለመተንበይ እንዲሁም ጥራትና መጠን ለመለካት የሚያስችሉ 4 ዓይነት የኮምፒውተር ፕሮግራሞች አጠቃቀም ብቃትን የሚያሳድግ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለፁት ተሳታፊዎች በሥልጠናው ቆይታ የሚያገኙት ዕውቀትም ሆነ እርስ በርስ የሚያደርጉት የልምድ ልውውጥ በዩኒቨርሲቲው ብሎም በሀገሪቱ በውኃው ዘርፍ ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አቅም የሚገነባና ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ ሠልጣኞች መካከል ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመጡት መምህር ኃይሌ አረፋይኔ ሥልጠናው የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ናሙና በመውሰድ ለመተንተንና ለመተንበይ የሚያስችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን እንዳውቅ ዕድል ሰጥቶኛል ብለዋል፡፡ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተሣታፊ የነበሩት መምህር አየነው ደሣለኝ እና መምህርት ሐናን ታደለ በበኩላቸው ከሥልጠናው ካገኙት እውቀት በተጨማሪ ከአሰልጣኙ የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ አጠቃቀም ልምድ የቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተሳታፊዎች የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀት ያበረከቱት ዶ/ር ፈለቀ በመዝጊያ ንግራቸው እንዳወሱት ሥልጠናው እውን እንዲሆን ከዓመት በላይ ጥረት የተደረገበትና ድርጅቱን በማሳመን ከፍተኛ ቅናሽ ተደርጎበት በግማሽ ሚሊየን ብር ወጪ የተከናወነ ነው፡፡ በመሆኑም ሥልጠናውን ወደ ተግባር መለወጥና ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ብሎም ሀገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሁሉም ተሣታፊ የውዴታ ግዴታ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡