አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ማዕከል ያደረገው የአርባ ምንጭ ሥነ-ህዝብና ጤና ልማት ፕሮግራም ‹‹ጥራት ያለው መረጃ ለተሻለ ጤና ልማት›› በሚል መሪ ቃል የግማሽ ቀን የባለድርሻ አካላት ውይይት ተደረገ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳወሱት ጥራት ያለው መረጃ ለማኅበራዊ ዕድገትና ለዕቅድ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም መረጃዎችን በአግባቡ የማደራጀት ልምድ እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ ፕሮግራሙ ዝርዝር የጤና መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው፡፡ የባለ ድርሻ አካላት ውይይት መካሄዱም ስለፕሮግራሙ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋትና ከሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማግኘት ረዳል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ፕሮግራሙን በተገቢው መንገድ ለመምራት በምርምር ማዕከል ደረጃ ለማቋቋም ዕቅድ ይዞ ፕሮፖዛል ማዘጋጀቱንም ም/ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ስኬታማ የማኅበረሰብና የሀገር ልማት ይኖር ዘንድ ጤናማ ዜጋን ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ይህንን ለማረጋጥና ተፅዕኖ አሳዳሪ የጤና ፖሊሲ ለማውጣት ተአማኒ መረጃ ማሰባሰቡ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ዲኑ አክለውም ኮሌጁ በሰው ኃይልም ሆነ በግብዓት ባልተደራጀበት የምሥረታው 2ኛ ዓመት ላይ ፕሮግራሙ ቢጀመርም በኅብረተሰቡ፣ በቀበሌ አመራር አካላት፣ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ድጋፍ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ በፈቃዱ ታሪኩ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የፕሮግራሙን ዓላማ፣ ዝርዝር ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችን፣ እንዲሁም በቀጣይ የታቀዱ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡ በመወያያ ፅሁፉ እንደተገለፀው በኢትዮጵያ ደረጃ ምርጥ የህብረተሰብ ጤና ምርምርና ክትትል ማዕከል መሆንን ዓላማ አድርጎ የተመሠረተውና ከኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር እና ከ CDC/Center for Disease Control and Prevention/ ጋር በመተባበር የሚሠራው የአርባ ምንጭ ሥነ-ህዝብና ጤና ልማት ፕሮግራም በሀገሪቱ ካሉ ስድስት የስነ ህዝብና ጤና ልማት ማዕከሎች አንዱ ነው፡፡

ፕሮግራሙ በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ማዕከል አድርጎ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተመረጡ 9 ቀበሌያት ተከታታይነት ያላቸው የሞት፣ የውልደት፣ የጋብቻ ሁኔታ እና የእንቅስቃሴ /የአካባቢ ለውጥ/ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከታቸው አካላት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

በመወያያ ጽሑፉ መነሻነት አስተያየታቸውን የሰጡ ተሣታፊዎች ቀደም ሲል በጤና ተቋማት በተሰበሰቡ መረጃዎችና በፕሮግራሙ በሚሰበሰቡ መረጃዎች መካከል ልዩነቶች የሚታዩ በመሆኑ በቀጣይ በመናበብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በሼሌ ሜላ ቀበሌ የፕሮግራሙ መረጃ ሰብሳቢ ተስፋጽዮን ንጉሡ በመረጃ ሰጪው ህብረተሰብ በኩል ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት በየቀበሌው የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄድ ይገባቸዋል ሲል አፅንዖት ሰጥቷል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች፣ የቀበሌ አመራሮች፣ የፕሮግራሙ መረጃ ሰብሳቢዎችና ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በቀጣይ ለፕሮግራሙ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡