በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በተዘነጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች /Neglected Tropical Diseases/ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የምርምርና ሥልጠና ማዕከል ማቋቋሙን ነሐሴ 02/2007 ዓ.ም ባካሄደው ወርክሾፕ ይፋ አድርጓል፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በመክፈቻ ንግግራቸው ምንም እንኳን በሀገራችን የህብረተሰብ ጤና በእጅጉ እየተሻሻለ ቢመጣም የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች ትኩረት በመነፈጋቸውና በመረጃ ክፍተት ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የጤና፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተሉ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሽታው በስፋት በሚታይበት አካባቢ በመገኘቱና ይህንን ክፍተት ለመሙላት ባለው ቁርጠኝነት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትና በጤናው ሴክተር የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ማዕከሉን ማቋቋሙን ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች ላይ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲሰራበት ቢቆይም በወሳኝ መረጃ እጥረት ምክንያት በተፈለገው መልኩ ለውጥ ሳይታይ መቆቱን በሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ የተዘነጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች የቴክኒክ አማካሪ ዶ/ር ፍቅረአብ ከበደ ይገልፃሉ፡፡ እንደ አማካሪው ገለፃ የዚህ ማዕከል መቋቋም የበሽታው ሥርጭት የሚታይባቸውን ቦታዎች በመለየት ለችግሩ እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ መፍትሄ ለመስጠትና ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ለሚጠይቁ አንዳንድ በሽታዎች አዳዲስ ግኝቶችን ለማሰባሰብ ብሎም በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ማዕከሉ በተዘነጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች ላይ እስከ አሁን የተከናወኑ የመከላከልና የማስወገድ ሥራዎች አጥጋቢ ውጤት ያላመጡበትን ምክንያት ለመለየት እንዲሁም መረጃቸው በትክክል የማይታወቅ በሽታዎችን የመረጃ ክፍተት መሙላትን ዓላማ አድርጎ እንደተቋቋመ ገልፀዋል፡፡ ማዕከሉ በተለይ ትኩረት የተደረገባቸውን የሆድ ጥገኛ ትላትሎች፣ የቆዳ ላይና የውስጥ አካል ካላዛር፣ ትራኮማ፣ ቢልሃሪዚያሲስ፣ ሌሽማኒያሲስ እና መሰል የቆላማ አካባቢ በሽታዎች የሥርጭት ሁኔታ ለማጥናትና መፍትሄ ለማፈላለግ ካውንስል አቋቁሞ ምሁራንን፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማትን፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አጋር ድርጅቶችን በማሳተፍ ለመሥራት መዘጋጀቱን ዲኑ አክለዋል፡፡

በእለቱ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ እና ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮ፣ ከሀገር በቀልና ከውጭ ሀገር አጋር ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተገኙበት ማዕከሉ በይፋ ተቋቁሟል፡፡