አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በWHaTeR /Water Harvesting Technologies Revisited / ፕሮጀክት በሰገን ህዝቦች ዞን ኮንሶ ወረዳ ያስገነባውን የያንዳ ፋሮ የጎርፍ መስኖ ቅልበሳ ግንባታ ነሐሴ 01/2007 ዓ.ም አስመርቋል፡፡

በኮንሶ ወረዳ ጃርሶ ቀበሌ አቋርጦ የሚያልፈው ያንዳ ፋሮ ደረቅ ወንዝ ለዓመታት አርሶ አደሩ ባልገመተው ወቅትና መጠን በጎርፍ ሲሞላ የበርካታ አባወራዎችን ማሣ በደለል አጥለቅልቆ ለችግር ሲዳርጋቸው መኖሩን ነዋሪዎቹ በምሬት ያስታውሳሉ፡፡ በ1996 ዓ.ም በአካባቢው በተከሰተው ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትም የወንዙ ከፍታ ሲቀንስ በአንፃሩ የደለሉ መጠን በመጨመሩ ውኃውን ወደ አርሶ አደሩ ማሣ በአግባቡ ለማድረስ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የያንዳ ፋሮ የጎርፍ መስኖ ቅልበሳ ሥራ ይህንን ችግር መነሻ ያደረገና የነዋሪዎቹን ምሬት መቋጫ ያበጀለት ፕሮጀክት ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለወረዳው ካለው ቅርበት እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህላዊ ዕውቀት ከግምት በማስገባት በWHaTeR ፕሮጀክት አማካኝነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ቴክኒካዊ ተፅዕኖዎችን አጥንቶ ወደ ሥራ መግባቱን በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አዳነ አበበ ይገልፃሉ፡፡ የጎርፍ መስኖ ቅልበሳው ውኃው በተዘረጉ የመስኖ መስመሮች በቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ ማሣ እንዲገባ በማድረግ በአግባቡ ለመጠቀም ሲያስችል ከፍተኛ ደለልንም የሚያስቀር ነው፡፡

በፕሮጀክት ትግበራው ወቅት የጎርፍ መጠን እና የመከሰቻ ጊዜን የመሳሰሉ አስፈላጊ መረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ያወሱት አስተባባሪው ችግሩን ለማቃለል ብሎም ቀጣይ ሥራዎችን ታሳቢ አድርጎ ዩኒቨርሲቲው በግንባታው አቅራቢያና የወንዙ መነሻ በሆነው የጊዶሌ ከፍተኛ ቦታዎች የአየር ጠባይ መቆጣጠሪያና መመዝገቢያ ጣቢያ / Automatic weather station/ ማቋቋሙን ገልፀዋል፡፡ በጣቢያው የነፋስ አቅጣጫና ፍጥነት፣ የአየር ግፊት፣ የሙቀትና የዝናብ መጠን በዘመናዊ መልኩ ተመዝግቦ በአራት ወራት አንዴ በኮምፒውተር በመታገዝ የሚሰበሰብ ሲሆን ከዚህ ቀደም መረጃዎቹ በሰው ሲመዘገቡ በግድየለሽነትና በአመዘጋገብ ስህተት የሚከሰቱ የህይወት፣ የጊዜና የገንዘብ ጉዳቶችን የሚያስቀር ነው፡፡

በኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለማየሁ ታዬ ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን ነባር ዕውቀትና ጉልበት መሠረት አድርጎ ሣይንሳዊና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መተግበሩን ተናግረዋል፡፡ ግንባታው የህብረተሰቡን ችግር ከመቅረፍና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በአፈር ጥበቃ የረዥም ጊዜ ልምድና ዓለም ዓቀፋዊ ዕውቅና ያለው የኮንሶ ማኅበረሰብ ባህላዊ ተሞክሮውን የሚያሳድግበት የዕውቀት ማሸጋገሪያ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

WHaTeR ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በውኃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን መገምገምን ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ፕሮጀክት ሲሆን በኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ማዕከል አድርጎ ባለፉት 4 ዓመታት በኮንሶ እና ሀላባ አካባቢዎች የውኃ ብክነት መቀነሻ ዘዴዎች ላይ ጥናትና ምርምሮች ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በፕሮጀክቱ በግንባታ ደረጃ የመጀመሪያው የሆነው የያንዳ ፋሮ የጎርፍ መስኖ ቅልበሳ ሥራ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ባለሙዎች የተገነባ ሲሆን 300 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ፡፡