የኢትዮጵያ የወባ ምርምር ትሥሥር /Malaria Research Network of Ethiopia/ ስድስተኛውን አውደ - ጥናት ከነሐሴ 19-20/ 2007 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡

 

የወባ ምርምር ትሥሥር የወባ ጥናትና ምርምሮች በጥራት እንዲካሄዱና በአግባቡ እንዲሠራጩ በአጥኚዎች፣ በጤና ባለሙያዎች፣ በፖሊሲ አውጪዎችና የወባ መቆጣጠር ሥራ በሚያከናውኑ ድርጅቶች መካከል ጥብቅ ቁርኝት ለመፍጠር ታልሞ ከአምሰት ዓመታት በፊት መቋቋሙን በአዲስ ኮንቲኔንታል የጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር አየለ ዘውዴ ይገልፃሉ፡፡ ትሥሥሩ በየዓመቱ አውደ ጥናት በማዘጋጀት ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ጥናት አቅራቢዎች የጥናት ውጤቶቻቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የወባ በሽታ ሥርጭት በስፋት በሚታይበትና ለወባ መስፋፋት አመቺ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድር ባለው አካባቢ በመገኘቱ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራና ምርምርን ከአገልግሎት ጋር በማጣመር ህሙማንን መርዳት እንዲቻል ታስቦ የዘንድሮው አውደ ጥናት በዩኒቨርሲቲው መካሄዱን ዶ/ር አየለ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር የምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ወዬሳ በበኩላቸው ማኅበራቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በየ3 ዓመቱ ብሔራዊ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያካሂድና የእውቀት ማስተላለፊያ መድረኮችን ለማጠናከር እንደሚሠራ ገልፀው ከመድረኮቹ አንዱ የሆነው ይህ አውደ-ጥናት በርካታ ተመራማሪዎች በጋራ የሚሠሩበትን ዕድል በመፍጠርና ምርምሮችን በማቀናጀት ለፖሊሲ ቀረፃ እና አዋጭ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልቶችን ለመንደፍ ይረዳል ብለዋል፡፡ ማኅበሩ በሀገሪቱ በተመረጡ ጠቋሚ ጣቢያዎች በተለይም በበሽታ አስተላላፊ ነፍሳት ቁጥጥር ስልቶች፣ ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮች የአገልግሎት ሁኔታ፣ የቤት ውስጥና የመስክ የፀረ ወባ መድሃኒት ርጭት ፣ የወባ መድሃኒቶች ውጤታማነት እና መሰል በወባ መቆጣጠር ሥራ የሚውሉ መከላከያ ዘዴዎች ውጤታማነታቸውን የመገምገምና የመቆጣጠር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወባ ላይ የሚሠሩ ምርምሮች በህክምናው ዘርፍ ከሚታዩ ችግሮች በተለይም ከመድሃኒት መላመድ ጋር ተያይዞ ለወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማጥፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ ገልፀው ለዚህም የተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ኮሌጁ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ወባን አንድ የምርምር መስክ በማድረግ በተለይም በመድሃኒቶች እና በህብረተሰብ ጤና ላይ ምርምሮችን እያከናወነ ሲሆን ትሥሥሩ ወጣት ተመራማሪዎች የምርምር ላይ ሥልጠና የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠር የተሻሉ የምርምር ሥራዎችን ለማበርከት የሚረዳ ነው፡፡

አሜሪካ መንግሥት የፕሬዚደንቱ የወባ ኢኒሽየቲቭ (USAID/PMI) በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ የወባ ምርምር ትሥሥር በዘንድሮው አውደ-ጥናቱ የፕሬዚደንቱ የወባ ኢኒሽየቲቭ ኤክስፐርትን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎች፣ የምርምር፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ከ15 በላይ የወባ ምርምሮችና ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት