በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም፣ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና በሌሎች ሀገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል

ምሁራኑና የአስተዳደር ሠራተኞቹ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ በሠጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከመስከረም 07 ጀምሮ የተሰጠው ስልጠና ዕቅዱን በብቃት እንዲያሳኩ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠሩንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ በሚደረገው ሂደት ግንዛቤያቸው እንዲያድግ እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዳስቻለም ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ትምህርትን ከማስፋፋትና የተማሪዎችን ቅበላ ከማሳደግ አንፃር የተሳካ ሥራ ማከናወኑን ገልፀዋል፡፡በውይይቱ ወቅት ጎልተው የወጡ የመልካም አስተዳደር፣ የግብዓት አቅርቦት እና የትምህርት ጥራት ችግሮችን በማስወገድም ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

በሚንስትር ዲኤታ ማዕረግ የኢፌዲሪ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታገሰ ጨፎ በሰጡት አስተያዬት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተገኙ ልምዶችን በመቀመር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተግቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በ ሦስት የሥልጠና ማዕከሎች ከ3 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ተካፋይ የነበሩ ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ሥልጠና ለነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንደሚሰጥ የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡