በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ 38 ለሚሆኑ የእንሰት ፓርክ ህብረት ሥራ ማህበር አባላት ከነሐሴ 29 - 30 /2007 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና የእንሰት ፓርክ ፕሮጀክት መስራች ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለፁት የእንሰት ፓርክ በጨንቻ ወረዳ በዶኮና በዶርዜ 12 ቀበሌያት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የኅብረት ሥራ ማህበሩ በአርሶ አደሮች በጎ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት በ2003 ዓ/ም ተቋቁሟል፡፡ የማኅበሩ ዓላማ እንሰትና ተያያዥ ምርቶችን መጠበቅና ዝርያዎቹ እንዲስፋፉ በማድረግ የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የእንሰት ምርት ምንም እንኳን ከ15 ሚሊየን ህዝብ በላይ የሚደግፍ ምግብ ቢሆንም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል ያሉት ፕሬዝደንቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠቀሜታው እየታወቀ በመምጣቱ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ጥናት መገባቱንና በቀጣይም በዲታ አካባቢ በሥፋት እንደሚሠራበት ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ለማህበሩ እዚህ መድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የማህበሩ አባላት፣ ለአ/ምዩ ባለሙያዎች እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው ለክርስቲያን ሰልፈር ግብረሰናይ ድርጅት የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከማህበሩ ጎን በመቆም  እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል እንደገለፁት የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ብቃት ያለው የእንሰት ተክል ተዋፅኦዎችን ለምግብነት ከመጠቀም ጀምሮ ለተፋሰስ ልማት፣ለአካባቢ ውበትና ለአየር ንብረት መስተካከል ከፍተኛ አስተዋፅን የሚያበረክት ነው፡፡እያንዳንዱ የእንሰት ፓርክ ማኅበር አባል በየጓሮው የሚያለማው እንሰት ምርት የመልክዓ ምድሩን ጤናማ የአስተራረስ ስርዓት በመጠበቅ የእንሰት ብዝሃነትን ለማስፋፋት የሚረዳ በመሆኑ የፓርኩ መቋቋም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሃገር በቀል የእውቀት ማዕከል የመጡት አቶ ለማ ከበደ እንሰት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በመሆኑ ያሉንን ዝርያዎች መጠበቅና ጥሩዎቹን አባዝቶ ለአርሶ አደሮች እንዲዳረስ ማገዝ፣ እንዲሁም ችግሮችን በመቅረፍ አስፈላጊውን ምርምር ለሚያካሂዱ ምሁራን ድጋፍ መስጠት እንደሚያሻ ጠቁመዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ምርት ለማሳደግና በእንሰት ምርት ምርምር ዙሪያ ምሁራንን ለማፍራት እያደረገ ያለው ተግባር ሊበረታታ ይገባዋል ብለዋል፡፡

 

የሥልጠናው ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ባህላዊ ዘዴን በመከተል ዝርያዎችን በማቀላቀል ይተክሉ እንደነበር ገልፀው በአሁኑ ወቅት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሚያደርግላቸው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ዝርያዎችን በመለየት በመስመር አራርቀው መትከል መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ዝርያዎችን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ የምናገኝበትን መንገድ በማመቻቸትም ዩኒቨርሲቲው ልዩ እገዛ አድርጎልናል ብለዋል፡፡