በ2008 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለተመደቡ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች በተዘጋጀው የአንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ለተማሪዎቹ ስኬታማነት ፋይዳ ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫና የልምድ ልውውጥ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ነባር ሴት ተማሪዎችም ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሥርዓተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መሠለ መርጊያ እንደገለፁት ዳይሬክቶሬቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዋናነት ሴቶች በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ሴት ተማሪዎች በሴትነታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በመፍታት፣ የምክር አገልግሎት በመስጠት፣  በሴቶች ክበብና በሴቶች ፎረም በማደራጀትና የትምህርት ድጋፍ አፈፃፀም በመከታተል የመማር ማስተማሩን ሥራ እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሥርዓተ- ፆታ ጉዳይ ለጥናትና ምርምር የሚጠቅሙ መረጃዎችን አጠናቅሮ ለሚመለከተው ክፍል የሚያቀርብ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችንም ይሰጣል፡፡
የፕሮግራሙ ተጋባዥ እንግዶች የሜሪ ጆይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ እና አርቲስት ሳምሶን ታደሰ /ቤቢ/ ለተማሪዎቹ የተለያዩ መልዕክቶችን ከግል ተሞክሮዎቻቸው ጋር እያዋዙ አቅርበውላቸዋል፡፡
ሲስተር ዘቢደር ተማሪዎች ከትንሽ ቦታ ተነስቶ ትልቅ ነገር ለመሥራት እንደሚቻል በማመን ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ደራሽ ለመሆን መትጋት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በበኩሉ ሁሌም ቅዠት ያልሆነ ትልቅ ህልም ይኑረን፤ ትክክለኛ የሕይወት ተልዕኮውን ለይቶ የሚያውቅ ሰው ህልሙን ወይም ራዕዩን እውን ማድረግ ይችላል በማለት ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይም አርቲስት ሳምሶን /ቤቢ/ ተማሪዎች የትምህርት ዘመናቸውን ባግባቡ በመጠቀም ያሉበትን ምዕራፍ በትዕግሥት ቢያጠናቅቁ በተማሪነት ወቅት የሚያጓጉዋቸውን ጉዳዮች ሁሉ በማሳካት በምርጫቸው መጠቀም እንደሚችሉ የበኩሉን ልምድ አካፍሏል፡፡ከያንዳንዳቸው የሕይወት ተሞክሮ ገለፃ በኋላም  ከተማሪዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
የ”Water Supply and Environmental Engineering” 5ኛ ዓመት ተማሪ ማህሌት በየነ የተማሪነት ህይወት ተሞክሮዋን ስታካፍል ሴት ተማሪዎች በግላቸው የመወሰን አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅሳ ይህንንም ለማዳበር የንባብ ባህልን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልፃለች፡፡ ለአብነትም አንባቢነቷ የተሻለ ግንዛቤና የውሰኔ ሰጪነት አቅም ፈጥሮላት ከአንባቢነት ወደ ፀሐፊነት በመሻጋገር የደረሰችው “አኬልዳማˮ የተሰኘው የመጀመሪያ የልቦለድ ሥራዋ ለህትመት ቀርቦ በአርትኦት ላይ እንዳለ ተናግራለች፡፡ “ጥቁር ሠንሠለትˮ የተሰኘ የፊልም ስክሪፕቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች፡፡ “ጊዜን ባግባቡ የሚጠቀም ሰው  ጊዜ የለውም!ˮ የምትለው ተማሪ ማህሌት ከትምህርቷ ጎን ለጎን በኢንፎኪን፣ ጄንደር፣ ገርልስና ሌሎችም ክበባት ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ ባሻገር በተማሪዎች መማክርትም ጊዜያዊ የዲስፕሊን ተጠሪ በመሆን እያገለገለች ነው፡፡
በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ 1ኛ የወጡ ሴት ተማሪዎች ከአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳምጠው በዕለቱ ንግግራቸው ተጋባዥ እንግዶቹ ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው ልምዳቸውን ለተማሪዎች ማካፈላቸው ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡም ለተማሪዎቹ በሥነ ልቡና መምህራን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ ከ400 በላይ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች የታደሙ ሲሆን በሌሎቹም ኮሌጆች ተመሳሳይ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡