በዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የተቋቋመው “የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች የትብብር ምርምርና ሥልጠና  ማዕከልˮ /Collaborative Research and Training Center for Neglected Tropical Diseases/ የሆድ ጥገኛ ትላትሎች እና ሺሽቶሶሚያሲስ/ቢልሃርዚያ/ በሽታ ህክምና ውጤታማነትን የሚፈትሽ ጥናት አካሂዷል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሆድ ጥገኛ ትላትሎች እና ሺሽቶሶሚያሲስ/ቢልሃርዚያ/ በሽታ ህክምና ዕድሚያቸው ከ5- 15 ለሚሆኑ ህፃናት በትምህርት ቤቶች በዘመቻ የሚሰጥ ሲሆን ከህክምናው በተጓዳኝ ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ ለትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና ለተማሪ ወላጆች ሥልጠና ያዘጋጃል፡፡
የህክምና ሽፋኑን ውጤታማነት እንዲሁም መድሀኒት ከመስጠት ባሻገር የሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎችን አስፈላጊነት ለመፈተሽ ጥናት በማስፈለጉ የምርምር ማዕከሉ ጥናቱን እንዲያካሂድ መመረጡን የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ ገልጸዋል፡፡ የማዕከሉን አቅም ለመፈተሽ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት እና Evidence Action ከተሰኘ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኝ ድርጅት የተወጣጡ ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው የዳሰሳ ጥናት አካሂደዋል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ መሠረትም ማዕከሉ በቂ አቅም እና መነሳሳት እንዳለው በመረጋገጡ ሥራውን ተረክቧል፡፡
ጥናቱ የሆድ ጥገኛ ትላትሎች እና ሺሽቶሶሚያሲስ/ቢልሃርዚያ/ በሽታዎች ሥርጭት፣ መተላለፊያ መንገዶች፣ የመድሐኒት አጠቃቀም፣ የመድሀኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች፣ የማህበረሰቡ የሥልጠናው አሰጣጥ ቅስቀሳ፣ የህክምናው ስታንዳርዱን መጠበቅ አለመጠበቅ ወዘተ… ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ 2 ሚሊየን 46 ሺህ 710 ብር የተበጀተለት ይህ ጥናት በሀገሪቱ 9 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 20 ወረዳዎች በእያንዳንዱ ወረዳ 10 በድምሩ 265 ትምህርት ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ 11 ሥራውን የሚቆጣጠሩ ሱፕርቫይዘሮች፣ 53 መረጃ የሚሰበስቡ ሞኒተሮች በድምሩ 64 ከዩኒቨርሲቲው የተወጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን መረጃ ሰብሳቢዎቹና ተቆጣጣሪዎቹ በቅድሚያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ወስደዋል፡፡
በዚህም መሠረት ጥናቱ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ ክልሎች እና በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተጠናቀቀ ሲሆን ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ እና ደቡብ ክልሎች በኮሚዩኒኬሽን ችግር እና በሌሎች አጣዳፊ መንግሥታዊ አጀንዳዎች ምክንያት ተቋርጧል፡፡
የምርምር ውጤቱ በተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች የሚታተም ሲሆን ለሀገሪቱ የፖሊሲ ቀረፃ ከፍተኛ አስተዋፅኦን የሚያበረክት ነው፡፡ በቀጣይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ ለጋሾች እና ባለ ድርሻ አካላት በሚገኙበት በዩኒቨርሲቲው የአንድ ቀን አውደ ጥናት ይዘጋጃል፡፡ በዓውደ ጥናቱ በተሰበሰቡት የመስክ መረጃዎች የተገኘው ውጤትና ተሞክሮ ለሚለከታቸው ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ይሆናል፡፡
ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ አቻ የምርምር ማዕከላት በንጽጽር የምሥረታ ዕድሜው አጭር ቢሆንም እንቅስቃሴውና የተገኘው ተሞክሮ እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ በኃይሉ ይህንን ዕድል ማግኘቱ የተቋቋመበትን ዓላማና የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ የሚያስተዋውቅ እንዲሁም የምርምር ማዕከሉን አቅም የሚገነባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሥራው የሚሠማሩ መምህራን ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲያሳድጉም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ይህንን በገንዘብ ከሚረዳው የእንግሊዙ ለንደን ሮያል ኮሌጅ ጋር በጋራ የመሥራት ዕድልም ይፈጥራል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት