በጤናው ዘርፍ ማህበረሰቡን ተዳራሽ ያደረጉ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ኮሌጁ አስታወቀ

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ተልዕኮውን ለማሳካት በቆላማና ደጋማ አካባቢዎች በሚከሰቱ በሽታዎች ዙሪያ እንዲሁም የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ ማህበረሰብ ተኮር አገራዊና አለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምሮችን በመምህራን እና በሙሉ ጊዜ ተመራማሪዎች በማከናወን ላይ መሆኑን የኮሌጁ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ ገልፀዋል፡፡  ከተከናወኑ ምርምሮች መካካል በጋሞ ጎፋ ዞን በሚገኙ ሆስፒታሎች የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የቅድመ ናሙና አያያዝ እና አተገባበር ላይ በተጠና ጥናት በሆስፒታሎቹ የሚታየው የህክምና ላቦራቶሪ በምርመራ ወቅትና ከምርመራ በኋላ የባለሙያው የምርመራ ውጤት አያያዝና አተገባበር እንዲሻሻል አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ በህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላቱ የአባላዘር በሽታዎችን በአግባቡ የማከም እና አጠቃላይ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ የተሰራ ምርምር ተጠናቆ ተደራሽ ሆኗል፡፡
በጨንቻ ወረዳ እድሜያቸው ከ5 -14 በሆኑ ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለ የሆድ ውስጥ ጥገኛ ትላትል በሽታ በርካታ ህጻናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ እያደረገ በመሆኑ የሆድ  ውስጥ ጥገኛ ትላትል በሽታ  በህጻናቱ እድገት እና ስነ ምግብ ላይ የተደረገው ጥናት በሽታውን በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤት አስገኝቷል፡፡
በተመሳሳይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት የሳንባ ምች በሽታ እና የበሽታው መንስኤዎች በሚል ርዕስ የዞኑን የጤና ተቋማት ማዕከል ያደረገው ጥናት የህብረተሰቡንና የጤና ባለሙያውን ግንዛቤ በመጨመር  የመከላከሉ ሥራ  ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል፡፡ 
በሌላ በኩል በዞኑ ቆላማና ደጋማ  አካባቢዎች በከፍተኛ ስርጭት ህብረተሰቡን በማጥቃት ላይ የሚገኙትን የተዘነጉ በሽታዎች ትራኮማ፣ ቢልሃርዝያ፣ የካላዛር፣ እና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎችን የሚያጠና የምርምር ማዕከል ተቋቁሞ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡
የጉበት በሽታ አምጪ ተህዋስ የሆነው የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ  እና ከእንስሳት ጋር ባለ ንክኪ የሚመጣው ቶክሶፕላዝማ ጎንዳይ ባክቴሪያ በእርግዝና ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፉ የሚያስችልና በአርባ ምንጭ ሆስፒታል የቅድመ-ወሊድ ክትትል በሚያደርጉ እናቶች ላይ የተደረገ ጥናት፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት ተጠቃሚዎች ላይ የደም ግፊት መጨመርና የስኳር ህመም መከሰት መንስዔዎች፣ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የኤች አይ ቪ በሽታ ስርጭት፣ የዩኒቨርሲቲው የምግብ ቤት ሠራተኞች የግል ንፅህና አጠባበቅ እና በምግብ ብክለት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች  ዙሪያ እየተደረጉ ያሉት ጥናቶች አበረታች ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት ምርምር ተኮር የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት “የምርምር ዉጤቶችን ወደ ማህበረሰብ ማድረስ” በሚል ርዕስ የፕሮጀክት አፃፃፍ የስልጠና ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡
ኮሌጁ ከ2006 - 2007 ዓ/ም ከ17 በላይ የምርምር ግኝቶችን  በ BMC (Bio Medical Central), Public library of Science, Hindawi Journal (Advances in public Health) እና በሌሎች አለም አቀፍና አገር አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትሟል፡፡