ለፀጥታና ደህንነት ፅ/ቤት ሠራተኞች ሚዛናዊ የውጤት ተኮር ሥርዓት ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ

በዩኒቨርሲቲው ሚዛናዊ የውጤት ተኮር ሥርዓት በቀጣይነት እንዲረጋገጥና ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጎለብት የሚያስችል ስልጠና በደህንነት ፅ/ቤት ለካምፓስ አስተባባሪዎች፣ ለግንባር ቀደም አባላት፣ ለሺፍትና ለ1 ለ 5 መሪዎች ከታህሳስ 14-18/2008 ዓ/ም ተሰጥቷል፡፡ በውጤት ተኮር ሥርዓት ግንባታ፣ በዲሲፕሊን ደንብና መመሪያ፣ በደህንነት ካሜራ እንዲሁም በሴንሰር አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና ከጽ/ቤቱና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች በመጡ ባለሙያዎች  ተሰጥቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለጹት መሰል ስልጠናዎች ለደህንነት አባላት መሰጠቱ በዩኒቨርሲቲው አስተማማኝ የሠላም ኃይል እንዲፈጠር ከማስቻሉም በላይ እንደተቋምና እንደአገር የተነደፉ እቅዶች እውን እንዲሆኑና የተጀመረው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዲሳካ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡   
ተቋሙ ያለምንም የፀጥታና ደህንነት ሥጋት ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጥና በውስጡ ያለው ማህበረሰብም ፀጥታና ደህንነቱ እንዲጠበቅ በውጤት ተኮር ምዘና ሥርዓት ግንባታ ላይ የአባላቱን ግንዛቤ ማዳበርና መተግበር ወሳኝ እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው የፀጥታና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ሻለቃ አበበ አማረ ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አስተማማኝ የሠላም ኃይል በመሆን  በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታ በመደራጀት ለተቋሙ ዕቅድ መሳካት ጽ/ቤቱ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም የውጤት ተኮር ሥርዓት ግንባታና ትግበራ የለውጥ ሥርዓት፣ የዲሲፕሊን አፈጻጸም ሥነ-ሥርዓትና ቅጣት ዓይነቶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በስልጠናው ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ከአምስቱ ካምፓሶች የተወጣጡ 100 የደህንነት ጽ/ቤት አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በተመሳሳይ  ጽ/ቤቱ ከደቡብ ክልል ፀጥታ ቢሮና ከጋሞ ጎፋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር ጋር በመተባበር የፀጥታ መረጃ አያያዝና አሰባሰብ ላይ ለጽ/ቤቱ ለመረጃ ባለሙያዎችና ለካምፓስ አስተባባሪዎች አባላት የሁለት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡