በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ጽ/ቤትና በተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተማሪዎች የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት አደረጃጀትን ለማጠናከር የሚያስችል የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ህዳር 28/2008 ዓ/ም ተሰጥቷል፡፡   የስልጠናው ዓላማ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተማሪዎች የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት እና  የ1 ለ 5 ቡድን  አደረጃጀት በጠራና በተስተካከለ ሁኔታ እንዲከናወንና ተሳታፊቹ የየራሳቸውን የ1 ለ 5 አደረጃጀት ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ በትክክል አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል መሆኑን በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ጽ/ቤት አስተባባሪና የአደረጃጀቱ ተጠሪ  ወ/ሮ ህይወት ፀጋዬ ገልፀዋል ፡፡
በኢንስቲትዩቱ 141 የመምህራንና 423 የተማሪዎች የሴክሽን ተጠሪዎች በ1 ለ 5 አደረጃጀት የሚገኙ ሲሆን በአደረጃጀቱ መሰረት የልማት ሰራዊቱ ተጠናክሮ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደባልቄ ዳልጮ  የትምህርትና ሥልጠና ሰራዊት አደረጃጀት፣ የህዝብ ክንፍ ምንነት እንዲሁም የልማት ቡድን(ሴክሽን)፣ የሴክሽን ኃላፊ መምህራንና የ 1 ለ 5 አደረጃጀት ኃላፊነትና ተግባራት ላይ በሰነድ የተደገፈ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከበላይ አመራር ጀምሮ በተዋረድ ያሉ የአመራር አካላት ለአደረጃጀቱ ትኩረት የሰጡ ቢሆንም ክትትልና ድጋፍ ከማድረግና ለምስጉን ኃላፊዎችና ግለሰቦች ዕውቅና ከመስጠት አኳያ ክፍተቶች እንደተስተዋሉ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡ ከተቋሙ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያያዥ የሆኑ  ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያቶች ላይ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በዚህም የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት በተለይ የ 1 ለ 5 አደረጃጀት በተማሪዎችም ሆነ መምህራን ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተገልጿል፡፡ በየሣምንቱና በየ15 ቀኑ ለሚደረጉ ሪፖርቶች በየደረጃውና በየወቅቱ ግብረ-መልሶች በተገቢው ሁኔታ ይሰጣል፡፡ ይህ የቴክኖሎጂና የትምህርት  ልማት ሰራዊት ግንባታ በዋናነት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ለማስቻል ነው፡፡
በፕሮግራሙ ላይ  የኢንስቲትዩቱ ማኔጅንግ ዳይሬክተር፣ የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ተጠሪ፣ የሴክሽን ተጠሪ መምህራን እና ተማሪዎች  ተገኝተዋል፡፡