የ1997 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው የሲቪል ምህንድስና ምሩቃን ከአስር አመታት በኋላ ለመገናኘት በገቡት ቃል መሰረት መስከረም/2008 ዓ/ም በአዲስ አበባ ባዘጋጁት የአብሮነት ፕሮግራም ለዩኒቨርሲቲው ከ30 በላይ መጽሐፍትን በስጦታ አበርክተዋል፡፡
መጽሐፍቱ በተለይም ለሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እንደ ማጣቀሻ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ምሩቃኑን በመወከል መጽሐፍቱን ለቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያስረከቡት አቶ እስከድል አበባው ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የእነዚህ መጽሐፍት እጥረት መኖሩን ማስተዋላቸው መጽሐፍቱን በሥጦታ ለማበርከት እንዳነሳሳቸውም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ከሲቪል ምህንድስና ባሻገር  የቀድሞ ምሩቃን (አልሙናይ) አባል በመሆን ቀጣይነት ባለው መልክ  ባለቸው አቅም ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን ራዕዩ ዕውን እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በመጽሐፍቱ ርክክብ ወቅት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምህንድስናና በሌሎችም ዘርፎች ምሩቃንን ለአገር በማበርከት የረጅም ዓመታት ልምድ ያካበተና በውሃው የትምህርት መስክ በሚሰጠው ትምህርትና ስልጠና በአፍሪካ ቀደምት ታሪክ ያለው ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎችም በውኃው መስክ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመጽሐፍት ልገሳው ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ስለሆነ መሰል ድጋፎችና አጋርነቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሦስት አስርት አመታት ጉዞው በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ከ30 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማበርከት ለአገር ዕድገት የራሱን አሻራ ማስቀመጥ የቻለ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡