ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ወጪና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት በማቅረብ ተማሪዎችን ለትምህርት፣ ለምርምር እና ለማህበረሰብ አገልግሎት ዝግጁ የማድረግ ተልዕኮ በማንገብ ውጤታማ ተግባር በመፈፀም ላይ መሆኑን የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በሥሩ ስምንት የሥራ ሂደቶችን በማቀፍ በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ግቢዎች በሚገኙ የማስተባባሪያ ጽ/ቤቶች አማካኝነት ከተማሪ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የምግብ፣ የመኝታ፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በቀጣይም የተማሪ ቁጥርና ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጁ ተጨማሪ መኝታዎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ የጤና ማዕከላትና የመዝናኛ ሥፍራዎች ተጠናቀው ሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ አሁን ያለውን ውስን የግብዓት ክፍተት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፉ ይታመናል፡፡
በያዝነው ዓመት በዋናው ግቢ 9,843፣ በጫሞ ግቢ 3086፣ በአባያ ግቢ 2,221፣ በነጭ-ሣር ግቢ 1,367 እና በኩልፎ ግቢ 890 በድምሩ 17,427 ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በመደበኛው መርሃ-ግብር በማስተናገድ በማስተባበሪያ ጽ/ቤቶቹ በኩል አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ለዚህም ተግባር ስኬታማነት ከ1,471 በላይ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ተሰማርተዋል፡፡