ከደጋማው የጉጌ ተራራ ግርጌ የሚነሳውና መዳረሻውን ጫሞ ሐይቅ የሚያደርገው ኩልፎ ወንዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሸክሞ የሚመጣውን አፈርና ደለል መጠን በመጨመሩ በተፋሰሱ አካባቢዎች እና በሐይቁ ሥነ ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እየጎላ መጥቷል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከልህቀት ማዕከላቱ አንዱ የውሃ ሃብት ልማትና አስተዳደር በመሆኑ እንዲሁም በኩልፎ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ በመገኘቱ የተፋሰሱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘‘Grand Kulfo Watershade Project’’ ቀርፆ የቅድመ ጥናት ሥራውን እያከናወነ ቆይቷል፡፡ የቅድመ ጥናቱ አካል የሆነውን የመስክ ጉብኝትም ከጥር 28-29/05 2008 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

የመስክ ጉብኝቱ ዓላማ ተመራማሪዎችና አመራር አካላት አካባቢውን የቅርብ ምልከታ በማድረግ ለፕሮጀክቱ የባለቤትነት ስሜት እንዲያሳድሩ እና ትኩረት እንዲቸሩት ለማነሳሳት እንዲሁም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወን መሆኑን የምርምር ዳይሬክተር ዶ/ ፋንታሁን /ሰንበት ገልፀዋል፡፡ በRiver taming፣ landscaping and beautification ፣ socio economic survey፣ hydro-meteorological እና land use planning and watershed development ቡድኖች በተዋቀረው የመስክ ጉብኝት የወንዙን መነሻ ተከትሎ በተፋሰሱ ያለውን የውኃ ጅረት መጠን፣ የገባሮቹን መገጣጠሚያ ቦታ የነዋሪውን አኗኗር፣ የአካባቢውን ስነ-ህይወትና ገጽታ ምልከታ አድርጓል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት የወንዙ መነሻ በሆነው በጉጌ ተራራ እና በሌሎቹም የተፋሰሱ አካባቢዎች ከህዝብ ቁጥር መብዛትና ከጥግግቱ ምጣኔ ጋር ተያይዞ ለእርሻ ሥራ መዋል የማይገባቸው ተራራማ ቦታዎች በተደጋጋሚ በመታረሳቸው፣ አስተራረሱም በአፈር ጥበቃ ዘዴዎች ያልታገዘ እና ዘመናዊነት ያልተላበሰ በመሆኑ፣ ደኑ በመመናመኑ እንዲሁም ሣሩ በግጦሽ በመጎዳቱ አፈሩ በከፍተኛ ሁኔታ እተሸረሸረ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተለይ በዝናብ ወቅት አፈሩ እየታጠበ በኩልፎ ወንዝ አማካኝነት ወደ ጫሞ ሀይቅ ስለሚገባ ለኢትዮጵያ ገበያ የአሳ ምርት በማቅረብ ከፍተኛ ድርሻ የሚያበረክተውን የሀይቁን ብዝሃ-ህይወት እያወከና ምርታማነቱንም እየቀነሰ ነው፡፡ ስለሆነም አፋጣኝ ሥነ ህይወታዊ ጥበቃ ሥራ በማከናወን አካባቢውን በመልሶ ማልማት እንዲያገግምማድረግና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተፋሰሱን ማልማት ወሳኝ ተግባር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህን ትልቅ ፕሮጀክት ቀርጿል፡፡

ፕሮጀክቱን ለመተግበር አካላዊና ሥነ-ህይወታዊ ብቻ ሣይሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ከግምትማስገባት ማኅበረሰቡ ጋር መቀናጀት ስለሚያስፈልግ የመስክ ጉብኝቱ የማስተዋወቂያ እና አጋሮችን የማፈላለጊያ አንዱ መንገድ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የተፋሰሱ አካባቢ ነዋሪዎችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል አማራጭ የገቢ ምንጭን ማዳበር፣ የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ ማልማትና ጥበቃ፣ መንገድና ትራንስፖርት የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የታችኛው ተፋሰስ አንድ አካል የሆነውን አርባ ምንጭ ከተማ ወንዙን ተከትሎ ለመዝናኛ እና ቱሪስት መስህብነት ማሳመር የፕሮጀክት ትግበራው አበይት ሥራዎች ናቸው፡፡ የጥናት ሥራው በጀት ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው የሚሸፈን ሲሆን ለቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ የተለያዩ አካላትን ድጋፍና ትብብር ይጠይቃል፡፡

 

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት