የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ 36 ጋዜጠኞችና ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 13 የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከየካቲት 28-29/2008 ዓ/ም በጂንካ ከተማ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል ፡፡

የስልጠናው ዓላማ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ባለሙያዎችን በሬዲዮና ቴሌቪዥን ዜና፣  በፕሮግራም  አዘገጃጀት እንዲሁም በልማታዊ ጋዜጠኝነት ንድፈ ሃሳብ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር የተሻለ የሚዲያ አሠራር ሂደት እንዲኖር ማስቻል  መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መ/ር አሰግደው ሽመልስ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው ዞኑ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኑ የዞኑና በሥሩ የሚገኙ ወረዳዎች የባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ባለሙያዎች የዞኑን ገፅታ ሊገነባ በሚችል መልኩ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ የሚያበቃ ነው፡፡ አስተባባሪው የልማታዊ ጋዜጠኛ  ምንነትና ዓይነት፣ ታሪካዊ አመጣጡ፣ አተገባበሩና ተግዳሮቶቹ፣ የጋዜጠኛውና የአድማጭ ሚና፣ ባህሪያቱ እንዲሁም የፍልስፍና ዳራውን አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አሸብር ልሳኑ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት በዞኑ ነባራዊ ሁኔታ ከሚዲያ አንፃር በቱሪዝም፣ በባህልና በልማት ዘርፍ በርካታ ተግባራት  እየተከናወኑ ቢሆንም የዜናና የፕሮግራም ዝግጅት ክህሎት ክፍተት በመኖሩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በቀጣይ ልማታዊ ተግባር ላይ በመረባረብ የዞኑን ሚዲያ ተወዳዳሪ ለማድረግና ዞኑን ለዓለም ለማስተዋወቅ የክህሎት ክፍተቶችን ለይቶ ሥልጠናዎችን መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጆርናሊዝምና ኮሚዩኒኬሽን መ/ር አቶ አሸናፊ ጉደታ የጋዜጠኝነት ፅንሰ ሃሳብና ስነ-ምግባሩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እውነትን አንጥሮ በማውጣት መናገር፣ ለህብረተሰቡ ታማኝና ነፃ መሆን፣ ጠቃሚ መረጃ ማቀበል፣ የዜናውን መጠንና ማስተላለፍ የተፈለገውን ሃሳብ ለአንባቢው በሚመችና በግልፅ መልኩ ማቅረብ የጋዜጠኝነት መርሆዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የዜና ምንነት፣ አፃፃፍና፣ የጥሩ ዜና ባህሪያት፣ ዜና ሲፃፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸውና ሊካተቱ  የሚገቡ ነገሮችን በስልጠናው ወቅት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በህዝብ ግንኙነትና በተግባቦት ስራዎች አተገባበር ላይ ስልጠና የሰጡት መ/ር ተስፋዬ አለማየሁ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የቆሙለትን ድርጅት ማስተዋወቅ፣ መልካም ገፅታን መገንባት እንዲሁም የሙያውን ክብር በማይጎዳ መልኩ እውነትን ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በህዝብና በመንግስት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው የሚሰሩ በመሆናቸው የስነ-ምግባር ጉድለቶች እንዳይኖሩ መጠንቀቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት የህዝብ ግንኙነት ከጋዜጠኝነት ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት እንዲያውቁ የረዳቸው ከመሆኑም ባሻገር  ከዚህ ቀደም በህዝብ ግንኙነት የሚሰሩትን ስራዎች ይበልጥ እንዲያጠናክሩና በዕውቀት ላይ ተመስርተው ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአቅም ውስንነት የሚስተዋልባቸው ባለሙያዎች በስልጠናው ጥሩ የግንዛቤ ለውጥ እንዳገኙና ለሥራቸውም ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት