ለዩኒቨርሲቲው መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች እንዲሁም ለቡድን መሪዎችና የዕቅድ ባለሙያዎች በፕሮግራም በጀት ይዘት፣ አሠራርና አስተዳደር የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና በ03/06/2008 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ Pictures.

 

የሥልጠናው ዓላማ ሀገራዊ አቅጣጫንና የዩኒቨርሲቲውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተግባርን መሠረት ያደረገ በጀት መደልደል እንዲቻል ግንዛቤ ማሳደግ መሆኑን የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ልዩ ረዳት አቶ ማሌቦ ማንቻ ገልፀዋል፡፡ ሥልጠናው እያንዳንዱ ሠልጣኝ በተዋረድ ያሉ ፈፃሚዎችን በማነቃቃት ለቀጣይ 2009 በጀት ዓመት ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራትን በመለየት በወጪ መደብ የተደገፈ ሥራ እንዲያከናውኑ ይረዳል፡፡

በሥልጠና ሰነዱ እንደተብራራው በጀት የአንድን መንግሥት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት የገቢና የወጪ ግምት በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ በዝርዝር በማሳየት ግቡን ያመላክታል፡፡ የፕሮግራም በጀት ውጤትን ለመለካት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነትን ለማስፈን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ የልማት እቅድን ከበጀት ጋር ለማስተሳሰር እና የመደበኛና ካፒታል ወጪዎችን ለማቀናጀት የሚያስችል ቁልፍ የበጀት አሠራር ሥርዓት ነው፡፡

የፕሮግራም በጀት ዝግጅት ሦስት ደረጃዎች ሲኖሩት የመጀመሪያው ‹‹የስትራቴጂክ ዕቅድ ማዕቀፍ ዝግጅት ደረጃ›› የሦስት ዓመታት የመሠረተ ልማት እና አገልግሎት አሰጣጥ ዕይታዎችንና የሚታወቁ፣ ሊለኩ የሚችሉ፣ የሚደረስባቸው፣ አግባብነትና የጊዜ ወሰን ያላቸው ዓላማዎችን የማዘጋጀት እና ፕሮግራሞችን የመመሥረት ተግባራትን ያካትታል፡፡ በደረጃ አንድ ተለይተው የተቀመጡ ዓላማዎችንና ፕሮግራሞችን ወደ ውጤት አመላካች ግቦች የመለወጥ እንዲሁም የየፕሮግራሙን የሦስት ዓመታት የወጪ ግምት የማዘጋጀት ተግባር በሁለተኛው የ ‹‹ውጤቶች፣ ግቦችና የሦስት ዓመት የወጪ ግምት ደረጃ›› የሚሠራ ይሆናል፡፡ ሦስተኛው ‹‹ዓመታዊ በጀት ዝግጅት ደረጃ›› የተግባራት ትንተና በማካሄድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የመለየትና ዓመታዊ የመደበኛ ዋና ተግባራት እና የካፒታል ፕሮጀክቶች የወጪ ግምት የማዘጋጀት ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡

የሥልጠናው ተሣታፊዎች በአስተያየቶቻቸው ሥልጠናው የ2007-2009 የፕሮግራም በጀት ዘመን የመጨረሻውን ዓመት ፕሮግራም በጀት ዝግጅት ለማጠናከር የሚረዳና የቀጣይ በጀት ዓመት የተግባራት ማስፈፀሚያ በጀት በወቅቱ ተመድቦ ወደ ሥራ መግባት እንዲቻል ግንዛቤያቸውን የሚያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሥልጠና ሰነዱ በቀረቡ መረጃዎች በግልጽ አልተቀመጡም ያሏቸውን ነጥቦች አንስተው ከመድረኩ ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡