በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤትና በህክምና ላብራቶሪ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት የወባ በሽታ የቤተ-ሙከራ ምርመራ ውጤት ጥራትን ለማስጠበቅ ከመጋቢት 12-15 /2008 ዓ/ም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

ስልጠናው የወባ በሽታ ምርመራ ወቅታዊነትና ጥራትን ለማስጠበቅ በዘርፉ የተሰማሩ የላብራቶሪ ባለሙያዎችን የሚያበቃና ወቅታዊ መረጃን አግኝተው አቅም እንዲፈጥሩ የሚያግዝ ነው፡፡ በአምስቱ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የተማሪዎች ክሊኒክ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ በግል ክሊኒክ ለሚሰሩ 30 የላብራቶሪ ባለሙያዎች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡

የወባ በሽታ ምርመራ ጥራትን ለማስጠበቅ የባለሙያውን አቅም ወቅታዊ ማድረግ እንደሚገባ በኮሌጁ የህክምና ላብራቶሪ ትምህርት ክፍል መምህር ጸጋዬ ዮሐንስ ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ የወባ በሽታ ምርመራ ቴክኒኮች/ Malaria Updated Diagnosis / ወቅታዊ በመሆናቸው ባለሙያዎች ከጊዜው ጋር እንዲራመዱ ለማድረግ በስራ ላይ ስልጠና መውሰድና በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት መፈተሽ አለባቸው፡፡ በሥራ ላይ ረጅም ጊዜ ከመቆየትና ከመላመድ የሚመጣ የባለሙያ ቸልተኝነትና የሙያውን የጥራት ደረጃ አለመጠበቅ የዘርፉ ክፍተቶች በመሆናቸው ስልጠናው ባለሙያዎች ራሳቸውን ፈትሸው በስታንዳርዱ መሰረት እንዲሠሩና በአፈጻጸም ወቅት የሚታዩ የክህሎት ደረጃ ልዩነቶችን ለመሸፈን ያስችላል፡፡

የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በመሆኑ ከስልጠና በኋላ የባለሙያዎች አፈጻጻም ውጤት መገምገምና በታዩ ክፍተቶች ላይ የማሻሻያ ስራዎች ተከትሎ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ከስልጠናው በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ የገለጹት ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ገዳይ የሆነውን የወባ በሽታ በመከላከል ረገድ የላብራቶሪ ባለሙያው ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበትና ሙያው የሚጠይቀውን የምርመራ ስታንዳርድ እንዲከተል ያስቻለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡