የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የመምህራንን የምርምር አቅም የሚያጎለብትና የምርምር ሥራ ጥራትን የሚያሳድግ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከመጋቢት 21 - 24/2008 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥልጠናው ሳይንሳዊ የምርምር ንድፈ ሀሳብ አዘገጃጀት/Scientific Proposal Development/፣ በቁጥር የሚሰበሰቡ መረጃዎችና ትንታኔዎች/Quantitative Research Analysis/ እና ለምርምር አጋዥ ሶፍትዌር አጠቃቀም /STATA Application Software/ የሚሉ ርዕሶችን ያካተተ ነው፡፡

የስልጠናው ዓላማ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ንድፈ ሀሳቦች በሳይንሳዊ ዘዴ ጥራታቸውን እንዲጠብቁ፣ የንግድና ምጣኔ ሀብት ምርምሮች በአብዛኛው በቁጥር የሚለኩ መረጃዎች በመሆናቸው የተለያዩ የቁጥር ትንታኔ ስሌቶችን /Econometrics/ እንዲጠቀሙ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ሶፍትዌሮችን እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው፡፡

የኮሌጁ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መምህር ጌታሁን ቀለመወርቅ እንደተናገሩት STATA Application Software በምርምር ወቅት በቁጥር ለሚሰበሰቡ መረጃዎች መለኪያና መተንተኛ ሲሆን የምርምር ሥራዎች ጥራት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ ስልጠናው በመምህራን የሚሰሩ ምርምሮች በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራታቸውን የጠበቁና ተቀባይነት ያላቸው፣ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ፣ ዩኒቨርሲቲውን የሚያስጠሩና ለህትመት ብቁ እንዲሆኑ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ያግዛል፡፡ መምህራን ለምርምር ሥራ እንዲነሳሱም ያደርጋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ለሚያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚዬም የኮሌጁ መምህራን በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ተሳታፊ ስለሚሆኑ በጥናትና ምርምር የሀገሪቱን ወቅታዊ የምጣኔ ሀብት መረጃ በቁጥር ለመሰብሰብ እንዲቻል የተሰጠው ስልጠና ወቅታዊና አቅም አጎልባች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎቹ በአስተያየታቸው በበርካታ ምክንያቶች አድካሚ የሆነውን የምርምር ስራ በቀላል መንገድ ጊዜና ወጪን በመቆጠብ መስራት የሚያስችል ስልጠና በማግኘታቸው በቂ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸውና በሥልጠናው መሠረት ምርምሮችን ለመስራት መዘጋጀታቸውን  ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው ከኢኮኖሚክስ፣ ከአካውንቲንግ፣ ከማኔጅመንትና ከቱሪዝም የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ 30 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡