የማኅበራዊ ሣይንስና ስነ- ሰብ ኮሌጅ ከጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት የትምህርት ክፍል እና ከኮሌጁ ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹Threats and Prospects of Natural Forest in Arba Minch›› በሚል ርዕስ ባከናወነው የቅድመ-ዳሰሳ ጥናት ላይ የአንድ ቀን የባለድርሻ አካላት ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የዳሰሳ ጥናቱ በአርባ ምንጭ እና አካባቢዋ እየደረሰ ያለውን የደን ጭፍጨፋ እና ውድመት በመከላከል ደኑን በዘላቂነት ለመጠበቅ እንዲቻል የተዘጋጀ ሲሆን የዓውደ ጥናቱ ዓላማ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባትን መፍጠርና በሚወሰዱ እርምጃዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት የትምህርት ክፍል መምህራን አቶ ሙሀመድ ሰይድ እና አቶ ታደሰ ደጀኔ ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት ደንና የደን አስተዳደር፣ የደን ሀብት ነባራዊ ሁኔታ በዓለም እና በኢትዮጵያ፣ በአርባ ምንጭና አካባቢዋ የደን ጭፍጨፋ መንስኤዎችና ተያያዥ ችግሮች፣ የአርባ ምንጭ የተፈጥሮ ደን ስጋቶችና የወደፊት እጣ ፈንታ እና የመፍትሔ እርምጃዎች የሚሉ ርዕሶች ተዳሰዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ እንደተመለከተው ደን ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ኦክስጅን ለማምረት፣ ለዘመናዊና ባህላዊ መድሃኒት ቅመማ፣ ለቱሪዝም መስህብነት፣ ወደ ከባቢ ዓየር የሚለቀቁና የዓለም ሙቀት መጨመርን ሊያባብሱ የሚችሉ ጋዞችን (Greenhouse Gases) በዋናነት የካርበንዳይኦክሳይድ ክምችትን ለመቀነስ እና የውኃ ዑደትን (Hydrological Cycle) ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

አርባ ምንጭ በተፈጥሮ ደን ሀብት የታደለች ብትሆንም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የተፈጥሮ ሀብቷ በእጅጉ እየተመናመነ እና የእጽዋት ስብጥሩም እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ማኅበራዊ ቀውሶች፣ የማገዶ እንጨት ለቀማና የከሰል ምርት፣ ገበያ ተኮር ዛፍ ቆረጣ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ፈጣን የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ መስፋፋት፣ ሥራ አጥነትና የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ለደኑ ሽፋን መቀነስና መመናመን በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ይህም በወቅቱ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተፈለገለት በአካባቢው ሥነ-ህይወታዊ፣ ከባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እሴቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

በዓውደ ጥናቱ ‹‹Causes for Challenges and Mitigation Measures on Vegetation in Nech Sar National Park›› በሚል ርዕስ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርዬ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ኑሯቸውን በደኑ ላይ የመሠረቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በማገዶና የግንባታ እንጨት ቆረጣ እና ከሰል ማክሰል በዓመት እስከ 10 ሄክታር ደን ይጠፋል፡፡ ህብረተሰቡ አማራጭ የኃይልና የገቢ ምንጭ እንዲጠቀም ግንዛቤውን ማሳደግና በቴክኖሎጂ መደገፍ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከክልሉ የደን ሀብት ቢሮ፣ ከዞን የደን ሀብት ጽ/ቤት፣ ከፍትህ አካላት፣ ከማረሚያ ተቋም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን አርባ ምንጭ ዲስትሪክት፣ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የሥራ ክፍሎች፣ ከሆቴሎች እና ሎጆች የተወጣጡ እንዲሁም በእንጨት ለቀማ ሥራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ተሣትፈዋል፡፡