የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት ከመንግሥትና ከግል ኮሌጆች ለተወጣጡ 38 መምህራን በGIS/ Geographic Information System/፣ በGPS/Global Positioning System/ እና በቴክኒካል ድሮዊንግ ሶፍትዌሮች ላይ ከጥር 7/2008 ዓ/ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

ከመንግስት ኮሌጆች ለአርባ ምንጭ፣ ካምባ፣ ጂንካ፣ ጨንቻ፣ ካራትና ኬሌ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም ከግል ኮሌጆች  ለአርባ ምንጭ ፓራሜድ፣ ሳንታ፣ ዙማ ኮሌጆችና ለአርባ ምንጭ መካነኢየሱስ ት/ቤት የቴክኒክና ሙያ መምህራን ሥልጠናው መሰጠቱን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ አዳነ ወ/መድህን ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሰርቬይንግና የGIS መምህርት መሰሉ አበራ ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት ሰልጣኞቹ የሶፍትዌሩን አጠቃቀም ተረድተው ከተመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ጋር አያይዘው ተግባራዊ እንዲያደርጉና ወደ አካባቢዎቻቸው ሲመለሱ ሌሎችን ማሰልጠን እንዲችሉ የሚረዳ ነው፡፡

የመምህራንን አቅም በቴክኖሎጂ ማጎልበት ለተማሪዎች ከሚማሩት ትምህርት ጋር የሚጣጣም ክህሎትን ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን የገለፁት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ታዬ ስልጠናው ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በመላመድ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠርና ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም በተለያዩ መስኮች በግል ለመስራትም ያስችላል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ በዛብህ በርዛ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ጊዜያቸውን ሰውተው ስልጠናውን በመስጠታቸው አመስግነው የስልጠናው ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የክህሎት ክፍተት ይታይ እንደነበረና በስልጠናው መሰረታዊ ጉዳዮችን ለመጨበጥ በመቻላቸው ያገኙትን ክህሎት በሙሉ ተነሳሽነት ለሌሎች ለማጋራት ብቁ መሆናቸውን ገልፀው  በቀጣይም አቅም ሊፈጥሩ በሚችሉ ሶፍትዌሮች ላይ  ስልጠናው ቢቀጥል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡