የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሎተሪ ሽያጭ ፕሮግራም ግንቦት 24/2008ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሴኔት አዳራሽ በድምቀት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ግድቡ የውጭ እርዳታ ሳይጠበቅ በህዝቦች አቅምና በሀገራችን መሃንዲሶች የሚሠራ በመሆኑ የይቻላል መንፈስ የታየበት የህዳሴ መግለጫ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በቦንድ ግዢ ያሳየውን ድንቅ መነሳሳት በሎተሪውም በመድገም የዕድሉ ተጠቃሚና የታሪክ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡

የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ በበኩላቸው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የቀጠናው ትስስርና ልማት መገለጫ፣ የህዳሴ ጉዟችን ስኬት ማሳያ፣ የኢትዮጵያዊነት ኩራት ማንጸባረቂያ እና አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ የሚያጠናክር የአብሮነታችን መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ዋጌሾ በውሃው ዘርፍ ያሉ ተሞክሮዎችን ሲገልጹ ‹‹በርካታ ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን ለመስኖ ሥራ፣  ለትላልቅ  የኃይል ማመንጫ እና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሀብታዊ ግልጋሎቶች ያውላሉ›› ብለዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጸ ምድርና በከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የታደለች በመሆኗ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ፖሊሲዎች ተነድፈው በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የቡድን መሪዎችና አስተባባሪዎች እንዲሁም የተማሪዎች ህብረት ሥራ አስፈፃሚዎች የሎተሪ ቲኬቱን ገዝተዋል፡፡ 40,000 (አርባ ሺህ) ብር የሚያወጡ 1000 ሙሉ የሎተሪ ዕጣዎች ቀርበው 456 ዕጣዎች የተሸጡ ሲሆን 18,240 ብር ተሰብስቧል፡፡ ቀሪዎቹ 544 የሎተሪ ዕጣዎች ለየኮሌጆች ተከፋፍለው ሽያጩ ተጠናቋል፡፡

የሎተሪ ሽያጭ ፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የግድቡ ግንባታ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑ እንደሚያኮራ ገልፀው ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡