ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከመምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞና ተማሪዎች ጋር ሚያዝያ 14 /2008 ዓ/ም ጉባኤ አካሂዷል፡፡

የጉባዔው ዓላማ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶችን በየጊዜዉ በመፈተሽ መሙላት እንዲሁም የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታንና የቅንጅት ሥራን ማጠናከር መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ገልፀዋል፡፡

በጉባኤው እንደተገለጸው በፀጥታና ደህንነት፣ በትምህርት ጥራት፣ በዉሀ አቅርቦት፣ በዶርም ንፅህና፣ በጤና አገልግሎት፣ በተማሪዎች ምግብ አገልግሎት ጥራት እንዲሁም በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ክፍተቶቶች ይስተዋላሉ፡፡ በቀጣይ ለሴት ተማሪዎችና ዝቅተኛ አፈፃፀም ላላቸዉ ወንዶች ልዩ ድጋፍ አጠናክሮ ለመስጠት፣ የትምህርት ይዘትን በአካዳሚክ ካላንደሩ መሠረት ለመሸፈን፣ የክፍለ ጊዜ ብክነትን ለማካካስ፣ ፈተናና ተከታታይ ምዘናን ለማመጣጠን፣ የFX መጠንን ለመቀነስ፣ በሬጅስትራር የምዝገባ ሂደት መንጠባጠብ እንዳይኖርና አሠራሩን ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን ለማስተካከል ከተማሪዎች ህብረት፣ከሠላም ፎረምና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸዉ ከንብረት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸዉን ጠቅሰዉ የባለቤትነት ስሜትን በማዳበር በአግባቡ መገልገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የዉሀ መስመርና የፍሳሽ ማስወገጃ ችግሮችን አስመልክቶም ከጥገና ክፍል ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ የሚበጅለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጉባኤዉ ከኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡