ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቡድን ከአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ አርባ ምንጭ ንዑስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትና ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችና በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በ13/09/08 ዓ/ም የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ‹‹አንድም ሰው በኤች አይ ቪ/ኤድስ እንዳይያዝ፣ እንዳይገለልና እንዳይሞት የድርሻችንን በመወጣት የሀገራችንን ህዳሴ እናረጋግጣለን!›› በሚል መሪ ቃል የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ተፅዕኖዎቹን ለመቀነስ የተቀመጠውን ሀገራዊ ዕቅድ ከዳር ለማድረስ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መስተጋብር በመፍጠር በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና በዙሪያቸው በሚገኙ ቀበሌያት የበሽታውን ስርጭትና አጋላጭ ባህሪያትን ለመለየት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡ ከጥናቱ በተገኘው ውጤት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በዳሰሳ ጥናቱ የተመለከቱ ችግሮችን ለመፍታትና የጋራ ግብ ለመጣል የፓናል ውይይቱ መዘጋጀቱን የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አለሙ ገልፀዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳና አጎራባች ቀበሌያት ለኤች አይ ቪ/ኤድስ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች፣ ተጋላጭ ወገኖችና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ በሰነዱ እንደተመለከተው የግንዛቤ ማነስ፣ ቸልተኝነት፣ ለሱስ መገዛት፣ ተገዶ መደፈር፣ የሴተኛ አዳሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች መብዛት እንዲሁም በሻይ ቡና እና በተለምዶ ‘ባናና ትሪፕ’ ሰበብ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጪ ማምሸት በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ለበሽታው አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በየቀበሌያቱ የሺሻ፣ የጫት መሸጫና መቃሚያ እንዲሁም ህገ-ወጥ ቪዲዮ ቤቶችና የወሲብ ፊልሞች መበራከት ለስርጭቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ በመሆኑ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ፊት በልዩ ልዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ለሀገር ዕድገት የላቀ ድርሻ የሚያበረክቱ እንደመሆናቸው በዕውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር ታንፀው እንዲሁም ከኤች አይ ቪ /ኤድስ ተጠብቀው ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተጨማሪ የአካባቢው ህብረተሰብ በቅንጅትና በባለቤትነት መንፈስ ሊሠራ ይገባል፡፡ በተለይም ኤች አይ ቪ/ኤድስ የህዳሴው አውታር የሆነዉን ወጣትና ጎልማሳዉን ክፍል በእጅጉ እያጠቃና ሀገር ተረካቢውን ትውልድ እየቀጠፈ በመሆኑ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ሥርጭቱን መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች ድጋፍና ክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ የግንኙነት ስርዓት በመዘርጋት በጋራ ወደ ተግባር መግባት፣ በዩኒቨርሲቲው ጥብቅ የሆነ የሰዓት እላፊ ቁጥጥር ማድረግ፣ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስን አስመልክቶ ቋሚ መልዕክቶችን በትምህርት ተቋማትና አካባቢዎች ማኖር እንዲሁም የተነሱትን ሃሳቦች እንደ ግብዓት ወስዶ ዕቅድ ማውጣትና የአፈፃፀም መርሃ ግብር ማዘጋጀት ተሳታፊዎቹ እንደ መፍትሔ ካቀረቧቸው ነጥቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በውይይቱ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳና ሳውላ ከተማ ካሉ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የተወጣጡ ተሳታፊዎች፣ የአጎራባች ቀበሌያት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡