የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ በአርባ ምንጭና አካባቢዋ ከሚገኙ ቀበሌያት የተወጣጡና ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ 30 ታዳጊ የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን አቋቁሟል፡፡

ሴቶች በስፖርቱ ዘርፍ በተለይም በእግር ኳስ ውጤታማ እንዲሆኑና ሀገራቸውን እንዲያስጠሩ ለማስቻል ቡድኑ መቋቋሙን የስፖርት አካዳሚ የቴክኒክ ረዳትና የታዳጊዎቹ አሰልጣኝ አቶ ማቲዎስ ማዜ ገልፀዋል፡፡

ታዳጊዎቹ በአሁኑ ሰዓት ከትምህርት ፕሮግራማቸው ጋር በማይጋጭ መልኩ የኳስ መግፋት፣ ማሳለፍ፣ ማንጠባጠብ፣ መጠለዝና መቆጣጠር የመሳሰሉ መሰረታዊ ልምምዶች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችና የስነልቦና ዝግጅት በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም አቅማቸውን ለመፈተሽ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው እንደገለፁት በውል ስምምነታቸው መሰረት ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው ስር ለ3 ዓመታት በስነ-ምግባር ታንፀውና ስፖርታዊ ጨዋነትን ተላብሰው እየሰለጠኑ የሚቆዩ ቢሆንም ጥሩ ብቃት ኖሯቸው የሚወስዳቸው ክለብ ካገኙ ዩኒቨርሲቲው በስምምነት ይሸኛቸዋል፡፡

ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ታዳጊዎችን በስፖርት ዘርፍ በማሰልጠን ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተተኪዎችን ከማፍራት አንፃር ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚው የክህሎት ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ በዛብህ አማረ እንደገለፁት አካዳሚው የሚያሰለጥናቸው ታዳጊዎች በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የፕሮጀክት ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች በመሆኑ ታዳጊዎቹ ትልቅ ዕድል እንዲያገኙ በር ከመክፈቱም ባሻገር አካዳሚው በሃገሪቱ ስፖርት ላይ የራሱን ሚና  እንዲጫወት ያስችለዋል ብለዋል፡፡

ታዳጊዎቹ በሰጡት አስተያየት አካዳሚው አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ከጎናቸው በመቆም የስፖርት ክህሎታቸውን በዕውቀትና በተግባር ታግዘው እንዲያጎለብቱ የሚያግዛቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ትምህርታቸውንና ስፖርቱን ጎን ለጎን በማስኬድና ለውጤት በመብቃት የሃገራቸውንና የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የቤተሰቦቻቸውን ስም ለማስጠራት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡