በ2008 የትምህርት ዘመን አንደኛ መንፈቀ ዓመት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት ፕሮግራም በሁሉም ካምፓሶች ተካሄደ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የፕሮግራሙ ዓላማ በውጤታቸው ብልጫ ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና በመስጠት ማበረታታትና ሌሎች ተማሪዎች አርአያቸውን በመከተል እንዲነቃቁ ማድረግ መሆኑን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ገልፀዋል፡፡ ሽልማቱ በተማሪዎች መካከል ጤናማ የትምህርት ፉክክር በመፍጠር እና ለተሻለ አፈፃፀም በማነሳሳት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡

በየኮሌጆቹ በተከናወኑት ፕሮግራሞች ከእያንዳንዱ ትምህርት ክፍል ከአንደኛ እስከ መጨረሻ ዓመት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማትና የዕውቅና ምስክር ወረቀት ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከዕለቱ እንግዶች እጅ ተቀብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ሴት ተማሪዎች ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የሽልማት ፕሮግራሙ የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና ውጤት ከመቼውም ጊዜ የተሻለ መሆኑ የታየበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የተመዘገበው አመርቂ ውጤት የመምህራንና የተማሪዎች የጋራ ጥረት ሲሆን ቀጣይነት እንዲኖረውና ሌሎች በርካታ ተሸላሚዎችን ለማፍራት የመረዳዳት መንፈስን ማዳበር፣ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊትን ማጎልበት እንዲሁም መሰል የማበረታቻ ፕሮግራሞችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ የበለጠ ለመሥራት የሚያነሳሳ እና በተማሪዎች መካከል ጤናማ የፉክክር መንፈስን የሚያዳብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ያስተማራቸውን ቤተሰብና ሀገራቸውን ለማገልገል ጠንካራ መሠረት የሚጥሉበት በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የሚኖራቸው ቆይታ በእውቀትና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ መሆን እደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ስልቶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን ክህሎት ያላቸውን ብቁ መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ላይ መመደብ፣ የትምህርት መሠረተ ልማት ማስፋፋትና ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማትን በትምህርት ቁሳቁስ ማደራጀት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም መሠረተ ልማቶችን በማሟላት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ ሙከራዎችና ቤተ መጽሐፍት በመገንባት እንዲሁም የመምህራንን አቅም በማጎልበት የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ጥረት እያደረገ ነው፡፡