‹‹ትውፊታዊ ዕውቀት፣ የባህል ብዝሃነትና ቅርስ አስተዳደር በኢትዮጵያ›› አራተኛው ሀገራዊ አውደ ጥናት ሰኔ 14/2008 ዓ/ም በማህበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ አዘጋጅነት ተከናውኗል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የዓውደ ጥናቱ ዓላማ በትውፊታዊ ዕውቀት፣ በባህል ብዝሃነትና ቅርሶች ጥበቃ ላይ ሳይንሳዊ ምክክር በማድረግ የምሁራንን ተሳትፎ ማሳደግና ለሚታዩ ችግሮች የመፍትሔ ሀሣብ ማስቀመጥ መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ እውነቱ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር እና የደቡብ ኢትዮጵያና ናይሎ ሰሃራ ባህል አጥኚ ዶ/ር ባይለየኝ ጣሰው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ችግር የራሳቸውን ባህልና ቅርስ አክብሮ ከመጠበቅ ይልቅ የምእራባውያንን ቋንቋ፣ ወግና ልማድ መከተል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሱርማና አኝዋክ ብሄረሰብ የግጭት አፈታት ዘዴን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች የሀገራቸውን ትውፊታዊ እውቀቶችና ቅርሶች በማጥናትና በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ብዝሃነት ሰፊ ጽንሰ ሀሣብ ሲሆን ብዝሃነት በሌለበት የተለያዩ ባህሎች፣ ልማዶችና ዕውቀቶችን ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ትውፊታዊ ባህሎች ለሥነ ጽሑፍና ለኪነ ጥበብ ሥራዎች ግብዓት የሚያበረክቱ ሲሆን በሌላ በኩል ቁሳዊ ባህሎች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህንን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በዘርፉ በቂ ጥናት ሊደረግና በወጉ ሊታወቁ ይገባል፡፡ በሀገራችን ሀገር በቀል እውቀትና ባህል ተገቢውን ትኩረት አላገኙም፡፡ ይህም አዕምሯዊና ኢኮኖሚያዊ ድህነትን የሚያስከትል በመሆኑ ሀገር በቀል እውቀትን ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር አስማምቶ ማስኬድ ይገባል ሲሉ ዶ/ር ባይለየኝ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ትውፊታዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍናና የሐይማኖት ብዝሃነት አከባበር በኢትዮጵያ››፣ ‹‹የግጭት አፈታት ሥርዓት በጌዲኦና ጉጂ ብሔረሰቦች››፣ ‹‹የህፃናት ፍልሰት በአማራ ክልል››፣ ‹‹የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት በትምህርት ጥራት ላይ ያለው አስተዋፅዖ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ››፣ ‹‹ትውፊታዊ የህክምና ዕውቀት በሺናሻ ብሄረሰብ››፣ ‹‹ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በአርቦሬ ማህበረሰብ›› እና ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች በምሁራን ቀርበዋል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፎቹን የተመረኮዙ አስተያየትና ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡